top of page

ሚያዝያ 29 2017 - የባህር ማዶ ወሬዎች

  • sheger1021fm
  • 1 day ago
  • 2 min read

ቀጣዩን የሮማ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ለመምረጥ የተለያዩ ሀገሮች የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያኖች ካርዲናሎች በቫቲካን ተሰብስበዋል ተባለ፡፡


በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ምርጫ ከ130 በላይ ካርዲናሎች እንደሚሳተፉ ቢቢሲ ፅፏል፡፡


ቀጣዩ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳስ እስኪመረጡም ካርዲናሎቹ ከውጭው አለም ጋር አንዳችም ግንኙነት እንደማያደርጉ ታውቋል፡፡

የቀድሞው የቤተ ክርስቲያኒቱ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ከ2 ሳምንታት በፊት በ88 ዓመታቸው ከዚህ አለም በሞት መለየታቸው ይታወቃል፡፡


የመጀመሪያው ምርጫ ዛሬ ዘግይቶ እንደሚከናወን በዘገባው ተጠቅሷል፡፡


በካርዲናሎቹ ምርጫ ማካሄዳ ፀሎት ቤት የጭስ ማውጫ ነጭ ጭስ ከታየ አዲስ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት መመረጡን የሚያሳይ ይሆናል፡፡


በአንፃሩ በጭስ ማውጫው ጥቁር ጭስ ቡልቅ ካለ የምርጫው ውጤት ገና ነው የሚል ትርጓሜ አለው ተብሏል፡፡



ሕንድ እና ፓኪስታን በጦር እየተካረሩ ነው፡፡


የሕንድ አየር ሀይል በፓኪስታን እና በፓኪስታን በሚተዳደረው የካሽሚር ግዛት ከባድ የአየር ድብደባ መፈፀሟን አልጀዚራ ፅፏል፡፡


CGTN እንደፃፈው ደግሞ በሕንድ የአየር ድብደባ 26 ሰላማዊ ሰዎች ተገድለውብናል ሲሉ የፓኪስታን የጦር ሹሞች ተናግረዋል፡፡


ሕንድ በድብደባዬ ዒላማ ያደረኳቸው የአሸባሪዎች ማሰልጠኛዎች ናቸው ማለቷን የፃፈው ደግሞ አልጀዚራ ነው፡፡


ፓኪስታን የህንድን ድብደባ ግልፅ ጦርነት ነው ብላዋለች፡፡


የፓኪስታን ሹሞች በደፈናው በርካታ የህንድ የጦር አውፕላኖችን መትተን ጥለናል ማለታቸው ተሰምቷል፡፡


የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሁለቱን አገሮች ውዝግብ እና ግጭት መስማቱ እጅጉን አሳፋሪ ነው ብለዋል፡፡


በቅርቡም ውዝግብ እና ግጭቱ እንደሚያበቃ ተስፋ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡


የተባበሩት መንግስታት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ የውዝግቡ ወደዚህ ደረጃ መሸጋገር በጣሙን አሳዝኖኛል ብለዋል፡፡


ሁለቱም አገሮች ከግጭት አባባሽ ድርጊት እንዲቆጠቡ ጠይቀዋል፡፡


ዋና ፀሐፊው ሕንድ እና ፓኪስተራን በየበኩላቸው የኒኩሊየር ቦምብ ታጣቂዎች ናቸው፡፡



የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ሕንድ እና ፓኪስታን ከውጥረት አባባሽ ድርጊቶች እንዲቆጠቡ ጥሪ አቀረቡ፡፡


በሕንድ ካሽሚር ግዛት የቱሪስቶች መዳረሻ ታጣቂዎች በፈፀሙት ጥቃት 26 ሰዎች መገደላቸውን ተከትሎ በሁለቱ አገሮች መካከል ከእለት እለት ውጥረቱ እየተባባሰ ነው፡፡


የጦር ዛቻዎችም መሰማት ከጀመሩ መሰንበታቸውን ካስፓር ዌብ ፅፏል፡፡


ሕንድ እና ፓኪስታን በየፊናቸው በካሽሚር ጉዳይ ስሜተ ስሱዎች መሆናቸው ይነገራል፡፡


በዚህችው ግዛት ጉዳይ ሁለቱ አገሮች በታሪክ ሁለት ጊዜ ታላላቅ ጦርነቶችን አድርገዋል፡፡


ጊዜያዊ ቁርቋሶዎቻቸውም የበረከቱ ናቸው፡፡


የተባበሩት መንግስታት ዋና ፀሐፊው በአሁኑ ውጥረት መባባስ በእጅጉ አዝኛለሁ ማለታቸው ተሰምቷል፡፡


ሕንድ እና ፓኪስታን በየፊናቸው የኒኩሊየር ቦምብ ታጣቂዎች ናቸው፡፡



የሱዳን መንግስት ከተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ ጋር የነበረውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አቋረጠ፡፡


የፕሬዘዳንት አብዱልፈታህ አል ቡርሃን መንግስት የባሕረ ሰላጤዋን አገር በወራሪነት መፈረጁን ሬዲዮ ታማዙጅ ፅፏል፡፡


የሱዳን መንግስት የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ የRSF ፈጥኖ ደራሽ ሀይልን ታስታጥቃለች በሚል ተደጋጋሚ ክስ እያሰማ ነው፡፡


በዚህም ኢሚሬትስ የአገራችንን ሉአላዊነት እየተዳፈረች ነው ብሏታል፡፡


የሱዳን መንግስት RSFን አማጺ ሲል ይጠራዋል፡፡


የሱዳን መንግስት ጦር እና RSF ጦርነት ማካሄድ ከጀመሩ ከ2 አመታት በላይ ሆኗቸዋል፡፡


ከጊዜ ወደ ጊዜ ሰብአዊ ቀውሱን እያከፋ የመጣው የሱዳኑ ጦርነት የቅርብ ጊዜ መቆሚያ ምልክቱ አይታይም፡፡


የኔነህ ከበደ

Comentários

Não foi possível carregar comentários
Parece que houve um problema técnico. Tente reconectar ou atualizar a página.
Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page