top of page

ሚያዝያ 16 2017 - የባህር ማዶ ወሬዎች

  • sheger1021fm
  • Apr 24
  • 2 min read

የእስራኤሉ የገንዘብ ሚኒስትር ቤዛሌል ስሞትሪች የጋዛ ሰርጥን እስከወዲያኛው ሙሉ በሙሉ ካልያዝነው ከመንግስት ሀላፊነቴ ለቅቄ እወጣለሁ ሲሉ አስጠነቀቁ፡፡


ስሞትሪች ለቅቀው ከወጡ የእስራኤል ጥምር መንግስት ለመፍረስ እንደሚገደድ ሚድል ኢስት ሞኒተር ፅፏል፡፡


የገንዘብ ሚኒስትሩ ጋዛን ሙሉ በሙሉ ካልተቆጣጠርነው ከእስራኤል መንግስት ለቅቄ ከመውጣት አልመለስም ሲሉ መዛታቸው ተሰምቷል፡፡

ቤዛሌል ስሞትሪች እጅግ የከረረ አቋም አላቸው ከሚባሉት የእስራኤል መንግስት ሹሞች አንዱ ተደርገው ይጠቀሳሉ፡፡


የገንዘብ ሚኒስትሩ የአሁኑ የጋዛ የጦር ዘመቻችን ሐማስን ሙሉ በሙሉ መደምሰስ እና የጋዛ ሰርጥን እስከወዲያኛው መያዝ መሆን ይኖርበታል ብለዋል፡፡


በእስራኤል የጋዛ የጦር ዘመቻ የተገደሉ ፍልስጤማውያን ብዛት ከ51 ሺህ 300 መብለጡን መረጃው አስታውሷል፡፡



በቱርክ የኢስታምቡልን ከተማ ባርገፈገፉት ከባድ ርዕደ መሬት 236 ሰዎች አካላዊ ጉዳት ገጠማቸው ተባለ፡፡


ኢስታምቡልን ያርገፈገፋት ከባድ ነውጥ በርዕደ መሬት መለኪያ /ሬክተር ስኬል/ 6 ነጥብ 2 ሆኖ መመዝገቡን አናዶሉ ፅፏል፡፡


ከ230 በላይ ሰዎች አካላዊ ጉዳት የገጠማቸው በመሬት ነውጡ ከፍተኛነት የተነሳ ተሸብረው ከየሕንፃው ወደ ምድር ለመወርወር ባደረጉት ሙከራ መሆኑ ታውቋል፡፡


ዋነኛውን ነውጥ ተከትሎ በርካታ መርገፍገፎች አጋጥመዋል ተብሏል፡፡


በነውጡ ያጋጠመ የቤቶች እና የመሰረተ ልማት መፍረስ ሪፖርት እንዳልተደረገ ተጠቅሷል፡፡


ያም ሆኖ ርዕደ መሬቱ በኢስታምቡል እና በአቅራቢዋ ነዋሪዎች ላይ ከባድ ፍራቻ እና መሸበርን መፍጠሩ ታውቋል፡፡


ከ2 አመታት በፊት የቱርክን ደቡባዊ እና የሶሪያን ሰሜናዊ ክፍል መትቶ የነበረው ነውጥ ከ50 ሺህ በላይ ሰዎችን መጨረሱን መረጃው አስታውሷል፡፡



የአሜሪካው ምክትል ፕሬዘዳንት ጄዲ ቫንስ በዩክሬይን ሰላም የማውረድ እቅዳችን በአጣዳፊ ፍሬ ካላፈራ ልንተወው እንችላለን ሲሉ አስጠነቀቁ፡፡


ቫንስ በሰላሙ ጉዳይ ሩሲያ እና ዩክሬይን በአስቸኳይ መስማማት ይኖርባቸዋል ማለታቸውን ቢቢሲ ፅፏል፡፡


የተፋላሚዎቹ ፍላጎት በእጅጉ ከመራራቁ የተነሳ የዩክሬይኑን ጦርነት በአጣዳፊ ስምምነት መቋጨቱ ዋዘኛ ተግባር እንዳልሆነ ሲነገር ቆይቷል፡፡


የዩክሬይኑ ፕሬዘዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ አጠቃላይ የተኩስ አቁም እንዲደረግ ሀሳብ አቅርበዋል ተብሏል፡፡


ሩሲያም በጦርነቱ ምክንያት የተጣለባት ማዕቀብ እንዲነሳላት እና ዲፕሎማሲያዊ መገለሉ እንዲቀርላት እንደምትሻ ተጠቅሷል፡፡


የአሜሪካ ሹሞች የዩክሬይኑን የሰላም ጥረት ልንተውም እንችላለን ማለታቸው እየደጋገሙት መሆኑን መረጃው አስታውሷል፡፡


ጦርነቱ ያለ ሁነኛ መፍትሄ ከ3 አመታት በላይ አስቆጥሯል፡፡


የኔነህ ከበደ


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…






Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page