top of page

ሚያዝያ 14፣2016 - በሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ የተነሳው የእሳት ቃጠሎ አሁንም ሙሉ ለሙሉ አልጠፋም ተባለ

ከሶስት ቀናት በፊት በሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ የተነሳው የእሳት ቃጠሎ አሁንም ሙሉ ለሙሉ አልጠፋም ተባለ

በሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ ውስጥ እና የተለያዩ አዋሳኞቹ ላይ ከሶስት ቀናት በፊት የእሳት ቃጠሎ መነሳቱ ተነግሯል።


በአካባቢው ነዋሪዎች እና የሰሜን ጎንደር ዞን አስተዳደር የጋራ ጥረት በፓርኩ የተለያዩ ክፍሎች፤ በተደጋጋሚ የተቀሰቀሰውን የእሳት ቃጠሎ መቆጣጠር እንደተቻለ፤ የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን የኮሙኒኬሽን እና የህዝብ ግንኙነት ጉዳዮች ስራ አስፈጻሚ ተወካይ ናቃቸው ብርሌው ነግረውናል።


አምባራስ በተባለው የፓርኩ ክፍል የተቀሰቀሰው እሳት ግን አሁንም እንዳልጠፋ ከአቶ ናቃቸው ሠምተናል።


የቃጠሎው መነሻ እየተጣራ እንደሆነ የነገሩን ተወካዩ ከህገ ወጥ የከሰል ማክሰል ተግባር ጋር በተገናኘ የተከሰተ ቃጠሎ ሊሆን እንደሚችል ግምት እንዳለ አክለዋል፡፡


እስከ አሁን ባለው ልምድ ይህ ወቅት በፓርኮች ላይ የእሳት ቃጠሎ ሊገጥም የሚችልበት ነው ያሉት አቶ ናቃቸው፤

የሚመለከታቸው ሁሉ ይህንኑ አውቀው ተገቢውን ጥንቃቄ በየአካባቢያቸው እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።


የሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ 412 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ስፋት ያለው ሲሆን እንደ ዋልያ፣ ቀይ ቀበሮ እና ጭላዳ ዝንጀሮ ያሉ ብርቅዬ የዱር እንስሳት መገኛ ነው።


ንጋቱ ረጋሣ




የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…




bottom of page