top of page

መስከረም 7 2018 - የውጪ ሀገራት ወሬዎች

  • sheger1021fm
  • Sep 17
  • 2 min read

የእስራኤል ጦር በጋዛ ከተማ የእግረኛ ጥቃት ማድረስ ጀመረ፡፡


የእስራኤል ጦር የጋዛ የእግረኛ ጥቃቱን የጀመረው ከተማይቱን በሚሳየሎች እና በከባድ መሳሪያዎች ሲደበድብ ከሰነበተ በኋላ እንደሆነ ቢቢሲ ፅፏል፡፡


በብዙ ሺህዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን የጋዛ ከተማን ለቅቀው እየወጡ ነው ተብሏል፡፡


ቀደም ሲልም በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ የከተማዋ ነዋሪዎች ከዚያ ለቅቀው እንደወጡ ተጠቅሷል፡፡

ree

የእስራኤል የጋዛ ዘመቻ በብሪታንያ እና በሌሎችም አገሮች በብርቱ እየተወገዘ መሆኑ ተሰምቷል፡፡


የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ ግን በሐማስ ጠንካራ ይዞታ ላይ ከባድ ዘመቻ ከፍተናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡


የጋዛ ከተማ ከአዲሱ ዘመቻ በፊትም ቢሆን በእስራኤል ተደጋጋሚ ድብደባ እንዳልነበረ ሆኖ ወደ ፍርስራሽ ክምርነት መለወጡን መረጃው አስታውሷል፡፡



የቻድ ፓርላማ የአገሪቱን ፕሬዘዳንት የአገልግሎት ዘመን ከ5 ወደ 7 አመታት ከፍ የሚያደርገውን ህገ መንግስታዊ ማሻሻያ ማፅደቁ ተሰማ፡፡


አንድ ፕሬዘዳንት በተደጋጋሚ መመረጥ እስከቻለ ድረስ ያለ ገደብ ስልጣን እንዲቆይ የሚፈቅድ ማሻሻያ እንደሆነ TRT አፍሪካ ፅፏል፡፡


በአሁኑ ወቅት የአገሪቱ መሪ ፕሬዘዳንት ማሐማት ኢድሪስ ዴቢ ናቸው፡፡


ማኅማት ኢድሪስ ዴቢ የአገሪቱ መሪ የነበሩት አባታቸው ኢድሪስ ዴቢ ከ4 ዓመታት በፊት በጦር ሜዳ በጉብኝት ላይ እያሉ ከተገደሉ በኋላ ህገ መንግስታዊ ባልሆነ መንገድ ተክተዋቸው እንደነበር መረጃው አስታውሷል፡፡


ከአመት በፊት በተደረገው ፕሬዘዳንታዊ ምርጫ አሸናፊ ሆነዋል፡፡


የፓርላማውም አብዛኛው መቀመጫ በሳቸው በሚመራው ገዢ የፖለቲካ ማህበር አባሎች የተያዘ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡



እስራኤል ትናንት በየመን የሁዳይዳን ወደብ በጦር አውሮፕላኖች መታቸው፡፡


የሁዴይዳ ወደብ የየመንን ሰሜናዊ ክፍል በሚያስተዳድሩት ሁቲዎች ይዞታ ስር የሚገኝ ነው፡፡


የጉዳቱን መጠን ባይዘረዝረውም የእስራኤል ጦር በሁዴይዳ ወታደራዊ ዒላማዎችን መትችቻለሁ ማለቱን አሶሼትድ ፕሬስ ፅፏል፡፡


የሁቲዎቹ ቃል አቀባይ ያህያ ሳሪ የአየር መከላከያዎቻችን የእስራኤልን የጦር አውሮፕላኖች በተገቢው ሁኔታ ተከላክለዋቸዋል የሚል መልዕክት በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው አኑረዋል ተብሏል፡፡


የየመን ሁቲዎች ከእስራኤል ጋር የጦር እልህ መጋባት ውስጥ ከገቡ ቆይተዋል፡፡


ሁቲዎቹ የኢራን የጦር እና የፖለቲካ ሸሪኮች መሆናቸው ይነገራል፡፡



ከ3 ወራት በፊት ከዚህ አለም በሞት የተለዩት የዛምቢያ የቀድሞ ፕሬዘዳንት ኤድጋር ሉንጉ ቤተሰቦች ቀብራቸውን ሕይወታቸው ባለፈባት ደቡብ አፍሪካ ለመፈፀም ያቀረቡት የይግባኝ አቤቱታ ውድቅ ተደረገባቸው፡፡


ቀደም ሲል የደቡብ አፍሪካ የስር ፍርድ ቤት የሉንጉ አስከሬን ወደ ዛምቢያ እንዲሸኝ ፈርዶ እንደነበር አናዶሉ አስታውሷል፡፡


የዛምቢያ መንግስትም በደቡብ አፍሪካ ፍርድ ቤት ሉንጉ የቀድሞ ፕሬዘዳንት በመሆናቸው መንግስታዊ የቀብር ሥነ ሥርዓት ይገባቸዋል ብሎ ሲከራከር ቆይቷል፡፡


ሉንጉ ሕክምና ሲከተሉባት በቆዩባት ደቡብ አፍሪካ ሕይወታቸው ያለፈው ከ3 ወራት በፊት ነው፡፡


የሉንጉ ቤተሰብ አሁን ካሉት የዛምቢያ መንግስት መሪዎች ጋር ባላቸው ፖለቲካዊ ውዝግብ የተነሳ የቀድሞው የዛምቢያ ፕሬዘዳንት እስካሁን ለቀብር እንዳልበቁ መረጃው አስታውሷል፡፡


የኔነህ ከበደ


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…




Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page