መስከረም 7 2018 - የተማሪዎች ጫማ እና ቦርሣ ፕሮጀክት የቆዳ ኢንዱስትሪውን ልማት እንዲደግፍ በሚል ነው በ2013 የተጀመረው
- sheger1021fm
- Sep 17
- 2 min read
በሀገር ውስጥ ባለሃብቶች የተያዙ አነስተኛ እና መካከለኛ የቆዳ ኢንዱስትሪዎች የሚያመርቷቸውን ጫማና ቦርሳዎች፤ ክልሎች ገዝተው ለተማሪዎች እንዲያቀርቡ ታስቦ የተቀረጸ ፕሮጀክት ነው።
በአንድ በኩል ለሀገር ውስጥ የቆዳ ፋብሪካዎች የገበያ ዕድል የመፍጠር ዓላማ ያለው ሲሆን በሌላ በኩል ፤ ተማሪዎች ልክ እንደ ደንብ ልብስ ሁሉ የሚያስፈልጓቸው ጫማና ቦርሳ እንዲሟሉላቸው የማድረግ ግብ ይዟል።
ወጣቶች የሀገር ውስጥ ምርትን መጠቀም እንዲለማመዱ ታስቦ የተጀመረም ነው።
መጀመሪያ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በኋላ ላይ ደግሞ ኦሮሚያ ፤ ሲዳማ እና ሃረሪ ክልሎች ለምርቶቹ ፍላጎት ማሳየታቸውን ተከትሎ ፕሮጀክቱ አገር አቀፍ እንዲሆን ተወስኗል፡፡
ፕሮጀክቱ 2013 ላይ ይፋ ሲሆን ሰፊ የማስተዋወቅ ስራ እንደተሰራ ያስታወሱት የቆዳ ኢንዱስትሪ ምርምር እና ፤ልማት ማዕከል ስራ አስኪያጅ አቶ ዙልፍካር አባጅሐድ ለተወሰኑ ተማሪዎች በመንግስት በጀት ጫማ ተገዝቶ መቅረቡንም ተናግረዋል።

ተማሪዎች የሀገር ውስጥ ምርትን መጠቀም በስፋት ከተለማመዱ በኋላ ምርቶቹን እየገዙ የማቅረቡን ሃላፊነት ወላጆች እንዲረከቡ የማድረግ ውጥን ተይዞ እንደነበር የሚያስታውሱት አቶ ዙልፍካር የተወሰኑ ስራዎች መሰራታቸውንም ነግረውናል።
ለፕሮጀክቱ የህግ ማዕቀፍ ማዘጋጀት ፤ ማህበረሰቡ ስራውን እንዲረከብ ማድረግ እና ተገቢውን በጀት መመደብ ላይ ግን ክልሎች እንዳሰብነው አልሆኑልንም ብለዋል አቶ ዙልፍካር።
የቆዳ ውጤቶች የሚያመርቱ ፋብሪካዎች በአብዛኛው በአዲስ አበባ እና ዙሪያዋ የሚገኙ መሆናቸውም ፕሮጀክቱን በመተግበሩ ሂደት ሌላው ፈተና እንደሆነ ተጠቅሷል።
ፕሮጀክቱን ስራ ላይ ከማዋል በፊት ፋብሪካዎቹ በሁሉም አካባቢዎች እንዲኖሩ ማድረግ ቅድሚያ እንደሚሰጠው ተረድተናል ብለዋል አቶ ዙልፍካር።
የቆዳ ውጤቶችን የሚያመርቱ ፋብሪካዎች እንዲስፋፉ የልማት አጋሮችም ድጋፍ ስለሚያስፈልግ በእሱ ላይም እየተሰራ ይገኛል ተብሏል።
አሁን ላይ በኢትዮጵያ በአመት እየተመረተ ያለው ጫማ 2 ነጥብ 4 ሚሊየን እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ።
በትምህርት ላይ ላሉ ሁሉም ተማሪዎች በአመት አንዴ እንኳን ይቅረብላቸው ቢባል 30 ሚሊየን ጥንድ ጫማዎች እንደሚያስፈልጉ ተነግሯል።
አንድ ተማሪ በአመት ሁለት ጊዜ ጫማ ቢገዛለት ደግሞ 60 ሚሊዮን ጥንድ ጫማ ማምረት ያስፈልጋል ተብሏል።
60 ሚሊየን ጥንድ ጫማዎችን ለማምረት አሁን ያሉትን የቆዳ ፋብሪካዎች ብዛት በአስር እጥፍ ማሳደግ እንደሚገባ ተጠቅሷል።
ንጋቱ ረጋሳ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s












Comments