መስከረም 26 2018 - የኢትዮጵያ እጣ ፈንታና መፃኢ እድል ከቀይ ባህር እና ከዓባይ ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው ተባለ፡፡
- sheger1021fm
- Oct 6
- 2 min read
ኢትዮጵያ በዓባይ እና በ #ቀይ_ባህር መካከል የምትገኝ በመሆኗ እጣ ፋንታዋ እና መፃዕይ እድሏም ከሁለቱ ውሃዎች ጋር በእጅጉ የተቆራኝ እንደሆነ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀስላሴ ተናገሩ፡፡
ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀስላሴ ይህን የተናገሩት ዛሬ መስከረም 26 ቀን 2018 ዓ.ም ከስዓት በኋላ በሁለቱ ምክር ቤቶች መክፈቻ ሥነ -ሥርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር ነው፡፡
6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን መክፈቻ ሥነ ሥርዓት ዛሬ ተካሄዷል፡፡
በመክፈቻው ላይ ንግግር ያደረጉት ፕሬዚዳንቱ አለም በተለዋዋጭ ሁኔታ ውስጥ እንደምትገኝ ተናግረው አህጉራችን አፍሪካም ሆነች ሀገራችን ኢትዮጵያ ከዚህ ዑደት ውጭ መሆን እንደማይችሉ አስረድተዋል፡፡

‘’በዚህ የአለም እውነታ ውስጥ ሰላምንና ደህንነትን ለማስጠበቅ፣ በአለም አቀፍ አህጉራዊ እና ቀጠናዊ ጉዳዮች ላይ ንቁ ተሳትፎ እንዲሁም የሰላም ተጽዕኖ ማሳረፍ ይገባናል’’ ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ለዚህም አራት ጉዳዮች በቀዳሚነት እንደሚከናወኑ ፕሬዚዳንቱ ጠቁመዋል፡፡
የመጀመሪያው ዜጋን ማዕከል ያደረገ ብሄራዊ ደህንነትን የማረጋገጥ ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡
‘’ብሄራዊ ደህንነት የአገራችንን ዳር ድንበር ማስከበር ብቻ ሳይሆን የዜጎቻችን ደህንነት እና ክብርንም ማስጠበቅ ይጨምራል’’ ሲሉ ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል።
በማናቸውም ቦታ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ደህንነት እና ክብር የሀገራዊ ደህንነት ጉዳይ ነው ያሉ ሲሆን ዜጎች በህጋዊ መንገድ መብታቸው ተጠብቆ የስራ እድል ተጠቃሚነታቸው እንዲረጋገጥ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ፕሬዚዳንቱ ጠቁመዋል፡፡
ሁለተኛው ‘’ኢትዮጵያ በዓባይ እና በቀይ ባህር መካከል የምትገኝ አገር ነች፡፡ እጣ ፋንታዋ እና መጻይ እድሏም ከሁለቱ ውሃዎች ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው ብለዋል፡፡’’ ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ፍትህን ባልተከተለ መንገድ እና ህዝብን ባላማከለ እንዲሁም ባላሳተፈ አግባብ ተገልላ እንደቆየች ፕሬዚዳንት ታዬ ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ ወደ እነዚህ ውሃዎች እንድትመለስ ፍትሃዊ የልማት ተጠቃሚ እንድትሆን መንግስት በመስራት ላይ እንደሚገኝ የጠቆሙት ፕሬዚዳንቱ ከሶስት አስርት ዓመታት በኋላ የባህር በር ጉዳይን የአለም አቀፍ መነጋገሪያ ማድረግ ተችሏል ሲሉ አስረድተዋል፡፡
በሶስተኛነት ፕሬዚዳንቱ ያነሱት ጉዳይ መንግስት ቅድሚያ ለጎረቤት የሚለው የውጪ ጉዳይ ፖሊሲ መርህ እንደሚቀጥል ነው፡፡
ባለፉት ዓመታት ከጎረቤት ሀገራት ጋር ግጭት እንዳይፈጠር እና ችግሮችም በሰላም እንዲፈቱ ጥረቶች ሲደረጉ ነበሩ ያሉት ፕሬዚዳንቱ ቀጠናዊ ትስስርን የሚያጠናክሩ የመሰረተ ልማት ስራዎችም ተሰርተዋል ሲሉ አስረድተዋል፡፡
በቀጣይም ኢኮኖሚውን የሚያሳድጉ እና የንግድ ልውውጦች እንዲጠናከሩ መንግስት እንደሚሰራ ጥቁመዋል፡፡
አራተኛው ደግሞ መንግስት የሃይል አሰላለፎች ውስጥ ሚዛኑን በመጠበቅ ትብብርን ለማጠናከር ይሰራል ብለዋል ፕሬዚዳንቱ በመክፈቻ ንግግራቸው፡፡
በአለም መድረኮች የኢትዮጵያ ተሳትፎ እና ተደማጭነት እንዲያድግ በአለም ወሳኝ ጉዳዮች ላይ ሀገሪቱ ደማቅ ድርሻ እንዲኖራት መንግስት በትኩረት ይሰራል ብለዋል፡፡
ለዚህም አስፈላጊውን ተቋማዊ ጥንካሬ፣ ፖሊሲ እና አቅጣጫዎች ተግባራዊ እንደሚደረግ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀስላሴ አስረድተዋል፡፡
ያሬድ እንዳሻው
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
🌐Website፡ https://www.shegerfm.com/
🎥YouTube https://tinyurl.com/37tux478
🟦Telegram https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📘Facebook፡ https://tinyurl.com/4tx8t8wm
💬WhatsApp ፡ https://tinyurl.com/ycxjmm3s
👔LinkedIn ፡ https://tinyurl.com/tyfaekvx
Comments