መስከረም 24 2018 - የሆረ ፊንፊኔ ኢሬቻ በዓል ዛሬ እዚህ በአዲስ አበባ ተከብሯል
- sheger1021fm
- Oct 4
- 1 min read
የሆረ ፊንፊኔ ኢሬቻ በዓል ዛሬ እዚህ በአዲስ አበባ ተከብሯል።
አባገዳዎች እና ሃደ ሲንቄዎችን ጨምሮ በጣም በርካታ ሰዎች አከባበሩን ታድመዋል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ በአሉ በደማቅ ስነ ስርዓት፤ በስኬትና በሠላም ተከብሯል ብሏል።
በዓሉ በስኬት እንዲከበር አስተዋጽኦ ላደረጉ ሁሉም ወገኖችም ምስጋናውን አቅርቧል።
የ2018 የሆረ ፊንፊኔ ኢሬቻ በዓል በጣም ብዙ ታዳሚዎች በተገኙበት ዛሬ እዚህ በአዲስ አበባ ተከብሯል።

ታዳሚዎች መሬ ሆ ወይም የጊዜ ኡደቱን ጠብቀህ ከጨለማ ወደ ብርሃን ስላሸጋገርከን እናመሰግናለን እያሉ ለፈጣሪያቸው ምስጋና በማቅረብ ወደ በዓሉ ማክበሪያ ቦታ መሄድ የጀመሩት ገና በማለዳው ነበር።
አባ ገዳዎች በምርቃት የበአሉን አከባበር አስጀምረዋል።
ዓመቱ የአንድነት ፤ የሠላም የይቅርታ እንዲሆን በምርቃታቸው ተመኝተዋል።
ሃደ ሲንቄዎችም እንዲሁ በበአሉ ላይ ተገኝተው በዝማሬ ለፈጣሪያቸው ምስጋና አቅርበዋል።
በዓሉ የተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦች የተገኙበትም ነው።
የየራሳቸው ባህል መገለጫ የሆኑ ሙዚቃዎቻቸውን አቅርበዋል።
የሆረ ፊንፊኔ ኢሬቻ በአል በአዲስ አበባ ሲከበር የዘንድሮው ለሰባተኛ ጊዜ ነው።
በነገው ዕለት ደግሞ በዓሉ በቢሾፍቱ ሆረ ሃረሰዴ ይከበራል፡፡
የዘንድሮው የኢሬቻ በአል እየተከበረ ያለው "ኢሬቻ ለሀገረ ማንሰራራት" በሚል መሪ ሃሳብ ነው።
በዓሉ የኦሮሞ ህዝብ ላለፈው መልካም ዘመን ለፈጣሪው ምስጋና የሚያቀርብበት ፤ ለመጪው ዘመን ደግሞ ምኞቱን የሚገልጽበት ነው።
ፈጣሪ በሰጠው ፀጋ መልሶ ፈጣሪውን የሚያመሰግንበት በዓልም ስለመሆኑ ተነግሯል።
ንጋቱ ረጋሳ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
🌐Website፡ https://www.shegerfm.com/
🎥YouTube https://tinyurl.com/37tux478
🟦Telegram https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📘Facebook፡ https://tinyurl.com/4tx8t8wm
💬WhatsApp ፡ https://tinyurl.com/ycxjmm3s
👔LinkedIn ፡ https://tinyurl.com/tyfaekvx








