ሐምሌ 8 2017 - ወጋገን ካፒታል ኢንቨስትመንት ባንክ በኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ላይ በሀገሪቱ የመጀመሪያውን የግምጃ ቤት ሰነድ እና የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ግብይት ማከናወኑን ተናገረ።
- sheger1021fm
- Jul 15
- 1 min read

ወጋገን ካፒታል ኢንቨስትመንት ባንክ የመንግስት የግምጃ ቤት ሰነድ እና የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ግብይት ሳደርግ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ሲል ለሸገር በላከው መግለጫ አስረድቷል።
ኢንቨስትመንት ባንኩ ግብይቱን ያካሄደው ሀምሌ 4 ቀን 2017 ዓ.ም በሸራተን አዲስ ሆቴል በተዘጋጀው የመንግስት ግምጃ ቤት ሰነድ እና የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ግብይት ይፋዊ ማስጀመሪያ ስነስርዓት ላይ መሆኑንም አስረድቷል፡፡
የኢንቨስትመንት ባንኩ በዕለቱ በአይነቱ የመጀመሪያ የሆነውን እና በአገበያዮች መካከል የተከናወነውን የግምጃ ቤት ሰነድ እና የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ግብይት በተሳካ ሁኔታ በመፈጸም ለሃገሪቱ የካፒታል ገበያ እድገት ጉልህ አስተዋፅዖ እያደረኩ እገኛለሁ ብሏል።
በተጨማሪም ኢንቨስትመንት ባንኩ ከኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ እና ማዕከላዊ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ግምጃ ቤት ጋር በመተባበር ከሰኔ 11 ቀን 2017 ጀምሮ የሙዓለ ንዋዮችን እና የግምጃ ቤት ሰነዶችን የግብይት ትዕዛዝ ከመቀበል እስከ ባለቤትነት ማዛወር ያለውን ስራ በተሳካ ሁኔታ የቀጥታ የሙከራ ግብይቶችን ሲካሂድ ቆይቻለሁ ብሏል።
በአሁኑ ወቅት ወጋገን ካፒታል ኢንቨስትመንት ባንክ አዳዲስ የካፒታል ገበያ አማራጮች በማቅረብ ስራ ላይ እየበረታ እንደሆነ አስረድቷል።
ንጋቱ ሙሉ












Comments