ሐምሌ 8 2017 - ስድስት ወር ባልሞላ ጊዜ መኪና አስመጣላችኋለሁ ካለን ኤል አውቶ የመኪና አስመጭ ድርጅት ጋር ውል ብናስርም እስካሁን መኪናው ሳይመጣ አምስት አመታትን አስቆጥረናል ሲሉ የአራራይ የታክሲ ዘርፉ ማህበራት ቅሬታ አቀረበ
- sheger1021fm
- Jul 15
- 1 min read

ኤል አውቶ የመኪና አስመጭ ድርጅት በበኩሉ መኪኖቹን ባልኩት ጊዜ ለደንበኞቼ ያላስረከብኩት በተለያዩ ምክንያቶች ነው ብሏል፡፡
ቅሬታ አቅራቢው አራራይ የታክሲ ዘርፍ ማህበራት ከአምስት አመታት በፊት ኤል አውቶ የመኪና አስመጭ ድርጅት ጋር ለታክሲ ስራ የሚሆኑ መኪኖችን እንዲያስመጣልን በማሰብ ውል አስረን ነበር ብሏል፡፡
ነገር ግን ከድርጅቱ በኩል በሚቀርቡ የተለያዩ ምክንያቶች መኪኖቹ እጃችን ላይ አልገቡም ያሉት ቅሬታ አቅራቢዎቹ የማህበሩ አባላት መጀመሪያ ስንዋዋል የነዳጅ መኪኖችን አመጣላችኋለሁ ብሎን ነበር ብለዋል፡፡
ከአመታት በፊት የነዳጅ መኪኖች በኤሌክትሪክ መኪኖች ይተኩ በተባለው መረጃ መሰረት ድጋሜ መኪኖቹን አስመጣላችኋለሁ ካለው ድርጅት ጋር ተፈራርመናል ይላሉ፡፡
ያንን ብናደርግም ግን እስከካሁን ድረስ መኪኖችን ከድርጅቱ እየተረከብን አይደለም ስንጠይቅም ትክክለኛ ምላሽ እየተሰጠን አይደለም ብለዋል፡፡
መኪና አስመጭ ድርጅቱ በሁለተኛው ውል መሰረት የኤሌክትሪክ መኪኖችን ሊያመጣልን ተዋውለን ነበር ነገር ግን ከውላችን ውጭ የሆኑ 300 መኪኖችን ነው ያመጣው ይላሉ ቅሬታ አቅራቢዎች፡፡
በዚያ ላይ የመጡትን ሚኪኖች ለአባላቱ እንድንወስድ የነገረን ከተዋዋልነው ገንዘብ በእጥፍ ጨምሮብን ነው ይህንን የመክፈል አቅም ደግሞ የለንም ብለዋል፡፡
በአራራይ የታክሲ ዘርፍ ማህበር በኩል ለተነሳው ቅሬታ መልስ ለማግኘት ወደ ኤል አውቶ የመኪና አስመጭ ጋር ደውለናል፡፡
ድርጅቱ መኪኖቹ በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ ደንበኞቹ እጅ አለመግባታቸውን አምኖ በተባለው ጊዜ ያለመምጣታቸው እና የመዘግየታቸው ምክንያትም ብዙ ነው ብሏል፡፡
መኪኖቹ ከዘገየባቸው ምክንያቶች መካከል መኪናውን የሚያመርተው ድርጅት በተለያየ ጊዜ ያመረታቸው የመኪና ምርቶች የቴክኒካል ችግር ስለነበረባቸው ደንበኞቼ ጋር ተነጋግሬ እንዲዘገይ በመወሰኑ፣ መኪኖቹ የቴክኒካል ችግሮች ማጋጠማቸው፣ ዶላር ዋጋ መጨመር፣ አበዳሪ ድርጅቶችን ማጣት ጨምሮ በሌሎችም ችግሮች ምክንያት መኪኖቹ ይደርሳሉ ተብለው ከተያዘላችው ጊዜ ገደብ እንዲዘገዩ ሆነዋል ብሏል ኤል አውቶ ኢንጅነሪንግ፡፡
ፋሲካ ሙሉወርቅ
ሙሉ ዘገባውን ያድምጡ….https://tinyurl.com/346rpam7








