ሐምሌ 30 2017 - ኢትዮጵያ ውስጥ በግል ከተያዙ ግዙፍና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች የሴቶች ተሳትፎ 25 በመቶ መድረሱን ጥናት አሳየ
- sheger1021fm
- Aug 6
- 2 min read
ሴቶች በሃላፊነት ቦታ ላይ ደግሞ ያላቸው ድርሻ አንድ አምስተኛ መሆኑን የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ያደረገው ጥናት አሳይቷል፡፡
የተጠቀሱትና ሌሎችም የጥናቱ ውጤቶች ሴቶች በስራ ላይ ያላቸው ተሳትፎ እያደገ መሆኑን ቢያሳይም ከወንዶች ጋር ሲነፃፀር ደመወዛቸው በ25 በመቶ ያንሳል ተብሏል፡፡
ሴቶች በተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች ያላቸው ተሳትፎ ፤ የሚመሯችው ድርጅቶች ውጤታማነትና የሚከፈላቸው ደመወዝ በጥናቱ ከተዳሰሱ ጉዳዮች መካከል ናቸው።

የጥናቱ ውጤቱ እንደ ሚለው እንደ ንግድ ባሉ የአገልግሎት ዘርፍ የተሰማሩ ሴቶች ከወንዶች ይልቅ ውጤታማ ሆነው ተገኝተዋል።
በግብርናው መስክ ደግሞ በተሻለ መልኩ ውጤታማ ናቸው የተባሉት ወንዶች ናቸው።
አምራች ዘርፉ ላይ በሁለቱም መካከል የጎላ ልዩነት እንደሌላ የኢንስቲትዩቱ ጥናት ያመለክታል።
ኢትዮጵያ ውስጥ በግል ከተያዙ ትላልቅ እና መካከለኛ አምራች ኢንዱስትሪዎች በሴቶች የተያዙት 25 በመቶዎቹ ብቻ ናቸውም ይላል ጥናቱ።
በጉልበት ስራዎች ላይ የተቀጠሩ ወንዶች ብዛት ደግሞ ከሴቶቹ በአስር በመቶ እንደሚበልጥ ጠቅሷል።
ጥናቱ በሃላፊነት ደረጃ ያሉ ሴቶችን ብዛት ከወንዶቹ ጋር አነጻጽሮ ያገኘውን ውጤትም ይፋ አድርጓል።
ሴቶች በአጠቃላይ ካሉ የሃላፊነት ቦታዎች የያዙት አንድ አምስተኛውን ብቻ ነው ብሏል።
ውጤቱ ቀደም ካለው ጊዜ መሻሻል መኖሩን እንደሚያሳይ የሚናገሩት የጥናት ቡድኑ መሪ ዶክተር አለበል ባይሩ አሁንም ብዙ ቀሪ ስራዎች እንዳሉም አመላካች ነው ብለዋል።
በወንድ እና ሴት ተቀጣሪዎች መካከል ያለውን የደመወዝ ክፍያ በተመለከተም ልዩነቱ እየጠበበ መምጣቱን፤ ነገር ግን አሁንም ወንዶች የተሻለ ተከፋይ ስለመሆናቸው ተጠቅሷል።
የደመወዝ ልዩነቱ እስከ 25 በመቶ እንደሚደርስ ነው የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት መረጃ የሚያሳየው።
ከሃያ አመት በፊት ልዩነቱ ወደ አርባ በመቶ እንደነበር የሚናገሩት ዶክተር አለበል አሁንም ግን ልዩነቱ ትንሽ የሚባል አይደለም ብለዋል።
ሴቶች በኢኮኖሚው ውስጥ ያላቸው ተሳትፎ በሚፈለገው መልኩ ለምን አልተሻሻለም? በሚል ላቀረብንላቸው ጥያቄም ተከታዩን ምላሽ ሰጥተዋል።
ሴቶች በኢኮኖሚ ውስጥ በሚገባቸው ደረጃ ተሳትፈው አስተዋጽኦቸው ከፍ እንዲል እንደ ብድር አቅርቦት ያሉ ድጋፎች ላይ መስራት ይገባል ተብሏል።
በአምራች ዘርፍ መሰማራት ለሚፈልጉ ደግሞ የግብአት አቅርቦት እንዲመቻችላቸው ጥናቱ ምክረ ሃሳብ ሰጥቷል።
በሳይንስና ቴክኖሎጂ የትምህርት መስኮች ገብተው በመማር በዚህ ዘርፍ ያላቸውን ተሳትፎ ማሳደግ ይገባልም ብሏል።
ሙሉ ዘገባውን ያድምጡ….. https://www.mixcloud.com/ShegerFM/45756/
ንጋቱ ረጋሳ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX
📌 WhatsApp: https://tinyu.com/ycxjmm3s












Comments