ሐምሌ 29 2017 - የወቅቱ የትንቢያ መረጃዎች ትክክለኛነት 75 በመቶ መሆኑን የኢትዮጵያ ሜቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ተናገረ
- sheger1021fm
- Aug 5
- 2 min read
Updated: Aug 6
ከትንቢያ መከታተያ መሳሪያዎች በሚገኘው መረጃ መሰረት የሚሰራው ትንቢያ አንዳንድ ጊዜ እስከ 90 በመቶም 100 በመቶም ትክክል የሚሆንበት ጊዜ ይኖራል ሲሉ የኢንስቲዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ፈጠነ ተሾመ ነግረውናል።
የወቅቱ የትንቢያ ትክክለኝነት ግን 75 በመቶ መሆኑን በመጥቀስ፤ ለምን ይሆን ፀሃያማ እንደሚሆን ተተንብዮ ደመናማ፤ ቀላል ዝናብ ይሆናል በተባለበት ቀን ከባድ ዝናብ አይነት የትንቢያ መዘበራረቅ የሚፈጠረው?
ይህ ከምን የመጣ ነው ያልናቸው ዳይሬክተሩ፤ እኛ አለም የደረሰበትን መሳሪያ ተጠቅመን ነው የምንሰራው ምናልባት የትንቢያ መዘበራረቅ ሊፈጠር የሚችለው በእውቀት ውስንነት፣በአለም አቀፍ ድንገተኛ ክስተትና በመሳሰሉት ምክንያቶች ሊሆን ይችላል ብለውናል።
የጠራ የትንቢያ መረጃዎች ለመሰብሰብ እንዲያግዘው ኢንስቲትዩቱ በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች 4 የአየር ሁኔታ መከታተያ ራዳሮች እየተከለ መሆኑን ነግሮናል፡፡
ራዳሮቹ ከተተከሉበት ስፍራ በ250 ኪሎ ሜትር ራዲየስ ውስጥ ያሉ የትንቢያ መረጃዎች መሰብሰብ የሚችሉ ናቸው፤ ራዳሮቱ በየትኛውም የዓለም ክፍል ደረጃውን የጠበቀ የትንቢያ መረጃ ለመሰብሰብ ጥቅም ላይ የሚውሉ ናቸው ያሉን የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ፈጠነ ተሾመ ናቸው፡፡

በሃገሪቱ የትንቢያ መረጃዎች የሚሰበሰቡባቸው ከ1372 በላይ ጣቢያዎች እንዳሉ የነገሩን ሃላፊው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በየ15 ደቂቃው መረጃዎችን ወደ ዋናው ቋት የሚልኩ አውቶማቲክ የመረጃ መሰብሰቢያ ጣቢያዎች እንዲሁም የከፍታ ቦታ የአየር ሁኔታ የሚሰበሰብባቸው ተጨማሪ 5 ጣቢያዎች በተለያዩ ቦታዎች መኖራቸውንም ጠቁመዋል፡፡
በእነዚህ ሁሉ የመረጃ መሰብሰቢያ ጣቢያዎች የሚገኘው መረጃ ተተንትኖ ነው የትንቢያ መረጃ የሚሰራጨው፡፡
አንዳንድ ከእነዚህ የመረጃ መሰብሰቢያ ጣቢያዎች ራቅ ብለው በሚገኙ ኢትዮጵያ አካባቢዎች እንዴት ባለ መልኩ ነው መረጃ የሚሰበሰበው? ያልናቸው ሃላፊው በአንድ በኩል የእነዚህን አካባቢዎች መረጃ የምናገኘው ከሳተላይት ምስሎች ከሚገኘው መረጃ ነው ብለውናል፡፡
በሌላ በኩል የመሰብሰቢያ ጣቢያዎች በሌሉባቸው የጠረፍ አካባቢዎች ያሉ መረጃዎች የሚሰበሰቡት ኢትዮጵያ ከጎረቤቶቿ ጋር በምታደርገው የአየር ትንቢያ መረጃዎች ልውውጥ መሆኑን ተናግረዋል።
በሃገራት መካከል የሚደረገው የአየር ትንቢያ መረጃ ልውውጥ በተለይ በሜዲቴራኒያን ባህር ላይ ያለው የሜትሮሎጂ ክስተት በኢትዮጵያ የአየር ጠባይ ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ የተመለከቱ መረጃዎች የሚገኙበት መንገድ ነው ተብሏል።
የአየር ጠባይ ድምበር ተሻጋሪ እንደመሆኑ እንደ ኬንያ ያሉ ሃገራት ከኢትዮጵያ ጋር ድምበር በሚዋሰኑባቸው ስፍራዎች ያሉ መረጃዎችን እርስ በእርስ መለዋወጥ እንዳለ የሜቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ፈጠነ ተሾመ ነግረውናል።
ኢትዮጵያ ድምበር ዘለል የትንቢያ መረጃዎችን መለዋወጥ የቻለችው የአለም የሜቴዎሮሎጂ ድርጅት አባል በመሆኗ ነው ያሉን አቶ ፈጠነ የወቅቱን የመረጃ ልውውጥ በተመለከተ ሲያስረዱም፤ አሁን ባለንበት የክረምት ወቅት በቀጠናው ምንም አይነት የኤልኒኖም ይሁን የላሊና ክስተት ስለማይኖር የሃገር ውስጥ የዝናብ መጠን መጨመር ሊያመጣው የሚችለው የጎርፍ አደጋ ካልሆነ በስተቀር በአለም የአየር ንብረት ተፅዕኖ ምክንያት የሚከሰት አደጋ አይኖርም ብለውናል፡፡
ሙሉ ዘገባውን ያድምጡ….. https://www.mixcloud.com/ShegerFM/547y45/
ምንታምር ፀጋው
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX
📌 WhatsApp: https://tinyu.com/ycxjmm3s