ሐምሌ 28 2017 - በአማራ ክልል ታውጆ የነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የጊዜ ገደቡ ከተጠናቀቀ ዓመት ቢያልፈውም ህገ ወጥ እስር እንደቀጠለ መሆኑ ተሰማ
- sheger1021fm
- Aug 4
- 2 min read
በአማራ ክልል ታውጆ የነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የጊዜ ገደቡ ከተጠናቀቀ ዓመት ቢያልፈውም ህገ ወጥ እና የተራዘመ እስር እንደቀጠለ መሆኑ ተሰማ፡፡
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን እንዳለው ከአማራ ክልል በተጨማሪ በኦሮሚያና በማዕከላዊ ኢትዮጵያም በወቅታዊ ሁኔታ በሚል ሰዎች በህገ ወጥ መንገድ አሁንም እየታሰሩ ነው፡፡
ከፍርድ ቤት ትዕዛዝ ውጪ በየፖሊስ ጣቢያው በተራዘመ እስር ላይ ያሉ ሰዎች መኖራቸውን ኮሚሽነሩ ብርሃኑ አዴሎ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ተናግረዋል፡፡
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሌለበት ሁኔታ በወቅታዊ ሁኔታ እያሉ መሰል ህገወጥ ድርጊቶችን መፈፀምም ተቀባይነት የለውም ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች በቀጠለው የትጥቅ ግጭት የሰላማዊ ሰዎች በሕይወት የመኖር መብታቸው እየተጣሰ እንደሆነ ኮሚሽነሩ ተናግረዋል፡፡
ለአካላዊ ጉዳት የሚዳረጉ እና ለተለያዩ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች የሚጋለጡም አሉ ተብሏል፡፡

በግጭቶች ምክንያት 7 ነጥብ 8 ሚሊየን ህፃናት ከትምህርት መራቃቸውንም ሰምተናል፡፡
በተጨማሪም በኢትዮጵያ ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ፣ በነፃነት የመደራጀት፣ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ፣ የመሳሰሉ መብቶችም አሳሳቢ ሆነው መቀጠላቸውን የኢሰመኮ አመታዊ የሰብአዊ መብት አያያዝ ሪፖርት አሳይቷል፡፡
የዳኝነትና ፍትህ የማግኘት መብትም እንዲሁ አሳሳቢ ነው ያሉት ኮሚሽነሩ የሰዎችን ፍትህ የማግኘት መብት የሚያጣብቡ ድብደባና ወከባን ጨምሮ የተለያዩ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እየደረሱ ነው ብለዋል፡፡
ከሰኔ ወር 2016 ዓ.ም እስከ ሰኔ 2017 ዓ.ም የነበረውን የሰብአዊ መብት አያያዝ በተመለከተ ሪፖርቱን ይፋ ያደረገው ኢሰመኮ እገታም ሌላው አሳሳቢ ጉዳይ ነው ብሏል፡፡
በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በቤኒሻንጉል፣ እና በጋምቤላ ክልሎች በተፈፀሙ እገታዎች ለማስለቀቂያ ብር መክፍል ባልቻሉ ታጋቾች ላይ እስከ መግደል የደረሰ ጥቃት ተፈፅሞባቸዋል ተብሏል፡፡
ታጋች ሴቶችም ተገደው ተደፍረዋል ሌላም የሰብአዊ መብት ጥሰት ደርሶባቸዋል ሲሉ ኮሚሽነሩ ተናግረዋል፡፡
የሰብአዊ መብት ሁኔዎችን በተመለከተም አስፈላጊ የማስተካከያ እርምጃ እንዲወስድ ለሚመለከታቸው አካላት ምክረ ሀሳብ መስጠቱንም ሰምተናል፡፡
በሌላ በኩል በሃገራዊ ምክክሩ የታጠቁ ሃይሎችም ትርጉም ያለው ተሳትፎ እያደረጉ አለመሆናቸው እና የሽግግር ፍትህ ሂደቱ መዘግየቱም እንደሚያሳስበው ኢሰመኮ በሪፖርቱ ተናግሯል፡፡
ኮሚሽነሩ አቶ ብርሃኑ በሪፖርቱ ማጠቃለያ ምክረ ሀሳቦችን ሰጥተዋል፡፡
መንግስትን ጨምሮ በትጥቅ ግጭት ውስጥ ያሉ ተዋናዮች ሁሉ የሰላማዊ ሰዎችን ሰብአዊ መብቶች እና አለም አቀፋዊ የሰብአዊ መብት መርሆዎችን እንዲያከብሩም አሳስበዋል፡፡
እንዲሁም ፖለቲካዊ አለመግባባቶችን በሰላማዊ መንገድ በንግግር እንዲፈቱም ጠይቀዋል፡፡
የሰሜኑ ጦርነት የተቋጨበት የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት አተገባበር ላይ እየተሰጡ ያሉ አሉታዊ አስተያየቶችም እንዲታረሙ አሳስበዋል፡፡
ለተፈናቃዮችም ያልተቆራረጠና ጊዜውን የጠበቀ የሰብአዊና ማህበራዊ አገልግሎቶች እንዲቀርቡላቸውም በምክረ ሀሳባቸው አሳስበዋል፡፡
ትዕግስት ዘሪሁን
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s
Comments