ሐምሌ 21 2017 - ቀሪው የክረምት ወቅት ጎርፍ ሊያስከትል የሚችል ከባድ ዝናብ ይጠበቃል ተባለ፡፡
- sheger1021fm
- Jul 28
- 1 min read
አዲስ አበባ ከተማን ጨምሮ በመላው የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ አካባቢዎች በቀሪዎቹ የሃምሌ ወር ቀናት እንዲሁም በነሃሴ ወር በሚኖረው ተከታታይነት ያለው ከባድ ዝናብ ጎርፍ ሊከሰት ይችላል ሲል የኢትዮጵያ ሜቴዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት በሰጠው ትንቢያ ተናግሯል፡፡
ለዝናብ መፈጠር ምክንያት የሆኑ የትንቢያ መረጃዎች እንደሚያሳዩት እየጣለ ያለው ዝናብ በመጠን እየጨመረ ስለሚመጣ በተለይ ለጎርፍ ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎች ላይ ጥንቃቄ እንዲደረግ አሳስቧል፡፡
በዚህ ወቅት በሚኖረው ዝናብ ውሃው ወደ ከርሰ ምድር ከመግባት ይልቅ በመሬት ላይ በመንሳፈፍ ወደ ቅፅበታዊ (ድንገተኛ) ጎርፍ የመቀየር እድል እንደሚኖረው የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዳይሬክተር ዶክተር አሳምነው ተሾመ ጠቁመዋል፡፡
የዝናቡ መጠን በአንዳንድን አካባቢዎች ጎርፍ ሊያስከትል ቢችልም ለክረምት ዝናብ ተጠቃሚ የሰብል አምራች አካባቢዎች፣ ለአካባቢ ጥበቃና ለመስኖ ስራዎች የተመቸ እንደሆነም ጠቅሰዋል፡፡

አዲስ አበባ በተለይ ንፋስ ስልክ ላፍቶና አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተሞች የጎርፍ ተጋላጭ በመሆናቸው እንዲሁም በሌሎችም የከተማዋ አካባቢዎች የጎርፍ ማፋሰሻ ቱቦች በቆሻሻ እንዳይደፈኑ በማድረግ ተገቢው ጥንቃቄ ይደረግ ተብሏል፡፡
አዲስ አበባን ጨምሮ በመካከለኛው የኢትዮጵያ ክፍል መደበኛና ከመደበኛ በላይ ከባድ ዝናብ፤ በደቡብና ምስራቅ ትግራይ፣ አፋር ክልል፣ ሰሜንና ደቡብ ወሎ፣ ሰሜን ሸፋና ምስራቅ ኢትዮጵያ ከመደበኛ በላይ የሆነ የዝናብ መጠን በክረምቱ ይጠበቃል፡፡
በክረምቱ አልፎ አልፎ የሚከሰት ካልሆነ በስተቀር ተከታታይነት ያለው ደረቃማ የአየር ጠባይ እንደማይኖር ኢንስቲትዩቱ በትንቢያው እወቁት ብሏል፡፡
ምንታምር ፀጋው
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s












Comments