top of page

ጥር  10፣2016  - የባህር ማዶ ወሬዎች


 

የሩሲያ ጦር በምስራቃዊ  ዩክሬይን ኪየቭ ያሰለፈቻቸውን የፈረንሳይ ቅጥረኛ ወታደሮችን ይዞታ በቦምብ አውድሜዋለሁ አለ፡፡

 

የሩሲያ ጦር ፈረንሳዊያኑ ቅጥረኞች ነበሩበት የተባለው እና የተመታው ስፍራ በሐርኪቭ ከተማ እንደሆነ አረብ ኒውስ ፅፏል፡፡

 

የፈረንሳይ መንግስት በዩክሬይንም ሆነ በሌላ የአለማችን አገሮች የፈረንሳይ ቅጥረኛ ወታደሮች የሉም ማለቱ ተሰምቷል፡፡

 

የሩሲያን ክስም መሰረተ ቢስ እና ባዶ ጩኸት ሲል ጠርቶታል፡፡

 

የሩሲያ ጦር በሐርኪቭ በርካታ የፈረንሳይ ቅጥር ወታደሮችን ገድያለሁ ቢልም ማስረጃ ግን አላቀረበም ተብሏል፡፡

 

ሩሲያ ሐርኪቭን ባልተቋረጠ ሁኔታ እየደበደበችው መሆኑ ይነገራል፡፡

 



 

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ የጋዛው ጦርነት ካበቃ በኋላ ነፃ የፍልስጤም መንግስት ይቋቋማል ብላችሁ እንዳትጠብቁ አሉ፡፡

 

የኔታንያሁ አስተያየት የተሰማው የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር ለእስራኤል እና ለፍልስጤማውያን ነባር ችግር ዘላቂው መፍትሄ የሁለት መንግስታት መሳ ለመሳ መኖር ማለቱን ተከትሎ እንደሆነ አናዶሉ ፅፏል፡፡

 

የመፍትሄ ሀሳቡ ከአሁኑ የጋዛ ጦርነትም በፊት ሲቀርብ የነበረ ነው፡፡

 

ሀሳቡ ፍልስጤማውያንም የነፃ አገር ባለቤቶች እንዲሆኑ የሚያስችል ነው ይባላል፡፡

 

ኔታንያሁ ግን ምንም ዓይነት የፍልስጤም መንግስት እንደማይመሰረት ለአሜሪካውያኑ ነግሬያቸዋለሁ ማለታቸውን ቻናል 12 የተሰኘው ቴሌቪዥን መዘገቡ ተሰምቷል፡፡

 

እስራኤል የአሜሪካ ሁነኛ አጋር እና ወዳጅ ብትሆንም በዚህ ጉዳይ ከአሜሪካ ጋር አቋማቸው ለየቅል እንደሆነ በዘገባው ተጠቅሷል፡፡

 

ሐማስ ከ3 ወራት በፊት ወደ እስራኤል በመዝለቅ ድንገት ደራሽ ጥቃት ከደረሰ ወዲህ እስራኤል በጋዛ ታላቅ የጦር ዘመቻ እያካሄደች ነው፡፡

 

በእስራኤል ዘመቻ አብዛኞቹ ሲቪሎች የሆኑ 25 ሺህ ያህል ፍልስጤማውያን መገደላቸው ይነገራል፡፡

 

 

በሜዴትሬኒያን የባህር አደጋ ገጥሟቸው የነበሩ 126 ሰዎች በምግባረ ሰናዮች ርብርብ መትረፋቸው ተሰማ፡፡

 

አደጋ የገጠማቸው በጀልባ ከሊቢያ ተነስተው ወደ አውሮፓ በማምራት ላይ የነበሩ ጥገኝነት ፈላጊዎች እንደሆኑ አልጀዚራ ፅፏል፡፡

 

ጥገኝነት ፈላጊዎቹ በወጀብ ስትመታ በነበረችዋ ጀልባ ለበርካታ ሰዓታት መንገላታታቸው ታውቋል፡፡

 

በዚህችው መከረኛ ጀልባ ላይ 30 አዳጊ ሕፃናት እና 1 ገና የተወለደ ጨቅላም ነበሩ ተብሏል፡፡

 

የምግባረ ሰናዮች የነፍስ አድን መርከብ ደርሳላቸው ከአሰቃቂው አደጋ መትረፋቸው ታውቋል፡፡

 

ስደተኞች በመናኛ ጀልባዎች በሚያደርጉት ባህር አቋራጭ ጉዞ አደጋ እንደሚጋገምበት ይነገራል፡፡

 

 

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ኢራን እና ፓኪስታን አንዷ በሌላዋ ላይ የሀይል ተግባር ከመፈፀም እንዲቆጠቡ መጠየቃቸውን ቃል አቀባያቸው ተናገሩ፡፡

 

ኢራን እና ፓኪስታን በየፊናቸው አንዷ በሌላኛዋ አገር አሸባሪዎች መሽገውባቸዋል ያሏቸውን ስፍራዎች በአየር መደብደባቸው የሰሞኑ ታላቅ ወሬ እንደሆነ ሬውተርስ ፅፏል፡፡

 

የተባበሩት መንግስታት ቃል አቀባይ ይሄ ጉዳይ ዋና ፀሐፊውን በእጅጉ አሳስቧቸዋል ብለዋል፡፡

 

በአየር ጥቃቶቹ በሁለቱም ዘንድ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ሞትና አካላዊ ጉዳት ማጋጠሙ ተነግሯል፡፡

 

በሁለቱ አገሮች መካከል በአሁኑ ወቅት ውጥረቱ እያየለ ነው ተብሏል፡፡

 

ዋና ፀሐፊው የሁለቱ አገሮች መንግስታት ችግሩን ከሀይል በራቀ ሁኔታ በንግግር መፍትሄ እንዲፈልጉለት መጠየቃቸው ተሰምቷል፡፡

 

ጉቴሬዝ ኢራን እና ፓኪስታን አንዷ የሌላዋን ሉአላዊነት እና የግዛት አንድነት ሊያከብሩ ይገባል ማለታቸው በዘገባው ተጠቅሷል፡፡

የኔነህ ከበደ

 


 

የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…

 

 

 

Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2024 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page