top of page

ግንቦት 8 2017 - ከተገነቡ እስከ ሠላሣ ዓመታት ያስቆጠሩ አራት የመስኖ ፕሮጀክቶች

  • sheger1021fm
  • 5 days ago
  • 2 min read

ከተገነቡ እስከ ሠላሣ ዓመታት ያስቆጠሩ አራት የመስኖ ፕሮጀክቶች የታሰበውን ያህል አገልግሎት እየሰጡ ባለመሆናቸው ኢትዮጵያ በአማካይ ከ48 ቢሊየን ብር በላይ በያመቱ እያጣች ነው ተባለ።


ከአራቱ ፕሮጀክቶች ሶስቱ አሁን ላይ ምንም አገልግሎት እየሰጡ እንዳልሆነ የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ትላንት በካፒታል ሆቴል ይፋ ያደረገው ጥናት አሳይቷል።


የመስኖ ግድቦች በባህሪያቸው ከፍተኛ ኢንቨስትመንት የሚጠይቁ ስራዎች መሆናቸው ይጠቀሳል፡፡


በኢትዮጵያም በከፍተኛ ወጪ የተገነቡ የተለያዩ ግድቦች በተለያዩ አካባቢዎች አሉ።


እነዚህ የመስኖ ግድቦች የወጣባቸውን ገንዘብ ያህል አገልግሎት እየሰጡ ነው ወይ? የሚለው ግን ጥያቄ እንደሆነ የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት በካፒታል ሆቴል ይፋ ያደረገው ጥናት ይጠቁማል፡፡


ኢንስቲትዩቱ ጥናቱን ያደረገው በከሰም ፤ ተንዳሆ ፤ ጎዴ እና አልዌሮ የመስኖ ግድቦች ላይ እንደሆነ ሠምተናል።


በዚህም 20 ሺህ ሄክታር መሬት በመስኖ ያለማል ተብሎ የተገነባው ከሰም ግድብ 2 ሺህ 700 ሄክታር ብቻ እያለማ እንደሚገኝ ተጠቅሷል።


60 ሺህ ሄክታር መሬት ያለማል ተብሎ የተገነባው የተንዳሆ ግድብ ደግሞ ምንም እያለማ አይደለም ተብሏል።


የጎዴ ግድብም 85 ሺህ ሄክታር ያለማል ተብሎ ቢታሰብም እያለማ ያለው አንድ ሺህ ሄክታር መሬት ብቻ እያለማ ይገኛል ሲሉ ፤ ጥናቱን ካደረጉት ባለሞያዎች አንዱ የሆኑት ዶክተር ታደሠ ኩማ ተናግረዋል።


አልዌሮ ግድብም አስር ሺህ ሄክታር ያለማል ተብሎ ነበር እስከ አሁን ምንም እያለማ አይደለም ብለዋል።


ከተገነቡ ከሰም ዘጠኝ ዓመት ፤ ተንዳሆ ስድስት ዓመት ፤ ጎዴ እና አልዌሮ ደግሞ ሰላሣ አመት ቢሆነችውም የታሰበላቸውን ያህል አገልግሎት ሳይሰጡ እስከ አሁን ዘልቀዋል ተብሏል፡፡


የተንዳሆ እና ከሰም ግድቦች የሚጠበቅባቸውን ያህል ባለማምረታቸው በአመት በአማካይ 43 ቢሊየን ብር እንደታጣ ጥናቱ ይፋ በሆነበት ወቅት ሲነገር ሰምተናል።

በጎዴ እና አልዌሮ ደግሞ 5.7 ቢሊየን ብር በያመቱ እንደሚታጣ ተነግሯል።


ከገቢው ባሻገር የመስኖ ግድቦች የታሰበውን ያህል አገልግሎት ባለመስጠታቸው ከገንዘቡ ባሻገር የስራ ዕድል እና ወደ ውጪ የሚላክ ምርትም ሳይገኝ መቅረቱ ተጠቅሷል።


የመስኖ ፕሮጀክቶቹ ለዚህ ሁሉ ዓመት አገልግሎት ያልሰጡባቸው የተላየዩ ምክንያቶች እንዳሉ ነው የሰማነው።


በተገነቡባቸው አካባቢዎች ካሉ ማህበረሰቦች የሚፈጠር ግጭት አንዱ እንደሆነ ጥናቱን ካደረጉት ባለሞያዎች አንዱ የሆኑት ዶክተር ታደሠ ኩማ ተናግረዋል።


በጎሳ መሪዎች ዘንድ ያለ አመለካከት እንዲሁ ም የጥገና እና የአስተዳደር ችግሮችም ሌሌቹ እንደሆኑ ዶክተር ታደሠ ነግረውናል።


የአካባቢው ማህበረሰብ አባላት ከፕሮጀክቶቹ ተጠቃሚ የሚሆኑበትን መንገድ ማፈላለግ ችግሩን ለመፍታት አንዱ መፍትሄ እንደሆነ የተናገሩት ደግሞ ሌላው የጥናቱ ተሳታፊ ዶክተር መኮንን በቀለ ናቸው።


መንግስትም ብዙ ገንዘብ የወጣባቸው እነዚህ ፕሮጀክቶች የታሰበላቸውን አገልግሎት እንዲሰጡ በትኩረት መስራት እንዳለበት ተጠቅሷል፡፡



ንጋቱ ረጋሣ


ሙሉ ዘገባውን ያድምጡ….


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…






Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page