top of page

ግንቦት 30፣2016 - በማረሚያ ቤት ያሉት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የዋስትና ጥያቄ ላይ ለመወሰን ፍ/ቤት ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጠ

  • sheger1021fm
  • Jun 7, 2024
  • 2 min read

በማረሚያ ቤት ሆነው ጉዳያቸውን እየተከታተሉ ያሉት የሕዝብ ተወካዮች እንዲሁም የአማራ ክልል እና የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አባላት የዋስትና ጥያቄ ላይ ለመወሰን ፍ/ቤት ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጠ።


የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሁለተኛ የሕገ መንግሥት እና ፀረ ሽብር ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ይህንን ትዕዛዝ ያስተላለፈው ዛሬ ግንቦት 29/2016 ዓ.ም በነበረው የፍርድ ቤት ውሎ ነው።


በዚህም ችሎቱ በፍትህ ሚኒስቴር የተደራጁ እና ድንበር ተሻጋሪ ጉዳዮች ዐቃቤ ሕግ ዳይሬክቶሬት ጄኔራል በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ክስ የተመሠረተባቸው 52 ግለሰቦችን ጉዳይ የተመለከተ ሲሆን በዛሬው ችሎት የቀረቡት 16ቱ ተከሳሾች ናቸው።


ከተከሳሾቹ ውስጥ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባሉ ክርስቲያን ታደለ፣ የአማራ ክልል ምክር ቤት አባል ዮሐንስ ቧያለው እና የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አባል ዶ/ር ካሳ ተሻገር ይገኙበታል፡፡

በአማራ ክልል በትጥቅ እንቅስቃሴ ላይ የሚገኙ ሌሎች ተከሳሾችም በሌሉበት በዚህ የክስ ዝርዝር ውስጥ ተካትተዋል።


ግለሰቦቹ ክስ የተመሠረተባቸው የፖለቲካ ርዕዮትን በኃይል ለማስፈጸም በማሰብ ከአማራ ፋኖ አንድነት ምክር ቤት ጋር በመደራጀት የሚል ይገኝበታል፡፡


ጉዳዩን ለመመልከት በተሰየመው የዛሬ ችሎት በተከሳሾች በኩል በርከት ያሉ አቤቱታዎች ቀርበዋል፡፡


የዛሬው ችሎት የተሰየመው የተከሳሾችን የክስ መቃወሚያ ለማድመጥና የእስረኞችን አያያዝ በተመለከተ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ሪፖርት ለማድመጥ ነበር፡፡


ተከሳሾች የክስ መቃወሚያቸውን በጽሁፍና በሲዲ ለፍ/ቤቱ አቅርበዋል፡፡


የሰብዓዊ መብት አያያዝን በተመለከተ ሪፖርት እንዲያቀርብ የተጠየቀው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ባለሙያዎች በበኩላቸው ባለፈው ከነበረው የፍ/ቤት ቀጠሮ የተሰጠን ጊዜ አጭር በመሆኑ የተሟላ ሪፖርት አላገኘንም ለዚህም ተለዋጭ ቀጠሮ ይሰጠን ሲሉ ጠይቀዋል፡፡


ፍ/ቤቱም በአቤቱታው መሰረት ኮሚሽኑ ምርመራውን አጠናቆ እንዲያቀርብ ሲል ለሰኔ 25 2016 ዓ.ም ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡


ተከሳሾች በበኩላቸው በማረሚያ ቤት ላይ ይፈጸምብናል ያሉትን አቤቱታ ለችሎቱ አስረድተዋል፡፡


ትልቅ ችግር የሆነብን የሚደርስብን የስነልቦና ጥቃት ነው ያሉት አቶ ዮሐንስ ቧያለው በማነታችን ምክንያት አድሎ ይደርስብናል፣ ቤተሰብ እንኳን እንዳናነጋግር ገደብ ተጥሎብናል ፣የጤንነታችን ሁኔታ ለመከታትል ተቸግረናል፣ በአጠቃላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እየተፈጸመብን ነው ብለዋል፡፡


አቶ ክርስቲያን ታደለ በበኩላቸው ከዚህ ቀደም ፍ/ቤቱ በሰጠው ትዕዛዝ የተሻሻሉ ነገሮች መኖራቸውን ጠቅሰው ነገር ግን አሁንም ማንነታችንን መሰረት አድርጎ በብሄራችን ምክንያት የተለያዩ በደሎች እየደረሱን ነው ለዚህም ፍ/ቤቱ በሌሎች ላይም ተመሳይ ነገር እንዳይገጥም አስተማሪ ማስጠንቀቂያ እንዲሰጥልን ሲሉ ጠይቀዋል፡፡


በተጨማሪም ተከሳሾች በተለያየ ጊዜ የተወሰዱባቸው ንብረቶች እብዲመለሱላቸው አቤቱታ ያቀረቡ ሲሆን ፍ/ቤት ከሳሽ አቃቤ ህግ ይህን እንዲያስተካክል ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡


አቃቤ ህግ በበኩሉ ለምርመራ በሚል በኤግዚቢትነት ከተያዙ ንብረቶች ውጪ ያሉት እንዲመለሱ እናደርጋለን ብሏል፡፡


የተከሳሽ ጠበቆች የዋስትና መብት የሚያሰጡ ምክንያቶችን በመጥቀስ

ተከሳሾች የዋስትና መብት እንዲፈቀድላቸው ሲሉ ለፍ/ቤት ጥያቄ አቅርበዋል፡፡


ከሳሽ አቃቤ ህግ በበኩሉ ከተከሳሾች ጋር በሌላ መዝገብ የተከሰሱና እስካሁን በቁጥጥር ስር ያልዋሉ ሰዎች በመኖራቸው ግለሰቦቹ በዋስ ቢለቀቁ ሌሎቹን ሊቀላቀሉ ስለሚችሉና የተከሰሱበት ወንጀል ከ15 ዓመት እስከ ዕድሜ ልክ ዕስራት የሚስፈርድ በመሆኑ የዋስትና ጥያቄው ውድቅ እንዲሆን ለፍ/ቤቱ ጠይቋል፡፡


የግራ ቀኙን ክርክር ያደመጠው ፍ/ቤቱ የዋስትና ጥያቄውን ለመወሰንና የአቃቤ ህግን መቃወሚያ ምላሽ ለማድመጥ ለሰኔ 12 2016 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡


በሌላ በኩል በአቃቤ ህግ ሶስት ተደራቢ ክሶች የቀረቡባቸው የቀድሞው ሰላም ሚኒስትር ዲኤታው አቶ ታዬ ደንደኣ   ምስክሮችን ቃልና የሰነድ ማስረጃ መርምሮ ውሳኔ ለመስጠት ፍ/ቤቱ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡


የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ የሕገ መንግሥት እና ህገመንግስት ስርዓት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀል ጉዳዮች ችሎት ዛሬ በዋለው ችሎት በተከሳሽ ላይ የቀረቡ ምስክሮችን ቃል አድምጧል፡፡


አቶ ታዬ በበኩላቸው የሳቸውም የባለቤታቸውም የባንክ ሂሳብ እንዳይንቀሳቀስ በመታገዱ ቤተሰባቸው ለችግር እንደተዳረጉ እና ፍ/ቤቱ ይህንን ለማስተካከል ለአቃቤ ህግ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ጠይቀዋል፡፡


በተጨማሪም በሁለት የመንግስት መገናኛ ብዙኃን የስም ማጥፋት ተፈጽሞብኛል ለዚህም ተቋማቱ ማስተካከያ እንዲያደርጉ እና ይቅርታ እንዲጠይቁ ሲሉ ለፍ/ቤቱ አቤቱታ አሰምተዋል፡፡


ፍ/ቤቱ የቀረቡ የሰነድ ማስረጃዎቹንና የምስክሮችን ቃል መርምሮ በጉዳዩ ላይ ብይን ለመስጠት ለሰኔ 18 2016 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠር ሰጥቷል።

Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page