በተገባደደው የካቲት ወር የመጀመሪያዎቹ ቀናት ጀምሮ የሀገር ውስጥ የቡና መገበያያ ዋጋ ከወትሮው በተለየ ጭማሪ ታይቶበታል፡፡
በአዲስ አበባ እንደየቦታውና እንደየ ደረጃው ልዩነቶች ቢኖሩትም ጭማሪው ግን በሁሉም የገበያ ስፍራዎች ተስተውሏል፡፡
ለአብነትም አንድ ኪሎ ቡና ከአንድ ወር በፊት ይሸጥበት ከነበረው ዋጋ ከ200 እስከ 300 ብር #ጭማሪ አሳይቶ ከሰሞኑ ከ800 አስከ 1000 ብር እየተሸጠ እንደሚገኝ ከሸማቾች ሰምተናል፡፡
ይህንን መነሻ በማድረግ በየዕለቱ የቡና እና የሌሎች ምርቶች የገበያ ዋጋን በማሰባሰብ ይፋ የሚያደርገው፤ የኢትዮጵያ ምርት ገበያን ጠይቀናል፡፡
በተቋሙ የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ስራ አስኪያጅ ዳዊት ሙራ፤ የቡና ዋጋ በየቀኑ እንደየገበያው የሚቀያየር መሆኑን ጠቅሰው ባለፉት ቀናት በቡና ላይ የታየው የዋጋ ጭማሪ የአቅርቦት እና የፍላጎት አለመመጣጥን አንዱ ምክንያት እንደሆነ ነግረውናል፡፡
ይህ የሚያጋጥመውም በዘመናዊ የግብይት ስርዓት ወደ ገበያው የሚገባው የ #ቡና መጠን ሲቀንስ ነው ብለውናል፡፡

በቡና ላይ የ #መንግስት ትኩረት ወደ ውጪ በመላኩ ላይ መሆኑንም አቶ ዳዊት ሙራ አስረድተዋል፡፡
መንግስት ከሀገር ወስጥ ፍላጎት ከሟሟላት ይልቅ ወደ ውጭ ልኮ የውጭ ምንዛሪን ማግኘት ይመርጣልም ተብሏል፡፡
በሀገሪቱ ያለው የቡና ተጠቃሚ ቁጥር ከፍተኛ መሆን፤ በኢትዮጵያ የቡና መሸጫ ዋጋ ለመወደዱ ሌላኛው ምክንያት እንደሆነም አንስተዋል፡፡
በኢትዮጵያ ከሚመረተው የቡና ምርት ግማሽ ያህሉ ለሀገር ውስጥ ተጠቃሚዎች እንደሚውልም መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
በቡና ግብይት ሰንሰለት የሚሳተፉ አካላት በዘመነ እና ስርዓት ባለው መንገድ እንዲራመዱ ቁጥጥር እና ክትትል በማድረግ የሀገር ወስጥ የቡና ዋጋ የበለጠ እንዳይወደድ ማድረግ ይገባልም ብለዋል ሀላፊው፡፡

በሰሞንኛ የግብይት ሂሳብ 1 ኪሎ ቡና አስከ 1000 ብር እየተጠሸጠ ቢሆንም በኢትዮጵያ ምርት ገበያ መረጃ ማሳወቂያ ላይ የየካቲት 26 ቀን 2017 ዓ.ም የቡና መገበያያ ዋጋ የታጠበው ለሀገር ቤት የሚቀርበው ቡና በ #ፈረሱላ 9917 ብረ መሆኑን ያሳያል፡፡ አንድ ፈረሱላ 17 ኪሎ ግራም እንደሆነም ይታወቃል፡፡
የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የገበያውን መረጃ ተከታትሎ በማሳቅ በነጋዴዎች እና በሸማቾች መካከል ግልጽ የመገበያያ ወጋ እንዲኖር ከማድረግ ባሻገር በዚህ ዋጋ ተገበያዩ ብሎ ዋጋ የመተመን ስልጣን የለውም፡፡
ኢትዮጵያ በቡና ምርት ከአፍረካ በአንደኛነት፣ ከዓለም ደግሞ ብራዚል፣ ቬትንሀም፣ ኮሎምብያ እና ኢንዶኔዢያን ተከትላ 5ኛ ደረጃ እንደተቀመጠች መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
ማንያዘዋል ጌታሁን
Comments