መንግስት ኢትዮጵያ ላይ አንባቢ ትውልድ እንዲጠፋ እያደረገ ነው ተባለ።
ይህ የተባለው የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር በመፅሐፍት ላይ ተጨማሪ እሴት ታክስ መጨመሩን ተከትሎ ባደረግው ውይይት ላይ ነው።
በወመዘክር መፃህፍት ቤት አንጋፋ ደራሲያን፣ አሳታሚዎች፣ የህግ ባለሙያዎች በተገኙበት በተደረገው ውይይት ከዚህ በፊት የነበሩ የመንግስት ከፍተኛ አመራሮች መፅሐፍት ከተጨማሪ እሴት ታክስ ነፃ እንዲሆን አድርገው እንደነበር ማህበሩ ጠቅሷል፡፡
አሁን ያለው መንግስት ግን በመፅሐፍት ላይ ተጨማሪ እሴት ታክስ እንዲጣል አድርጓል ብሏል።
በመንግስት አካባቢ በድርሰት የሚታወቁ ሰዎች ቢኖሩም ችግሩን እያወቁ ችላ ብለውታል ተብሏል፡፡
በተለያዩ ጊዜያት መንግስት አብያተ መፅሐፍት እና ትምህርት ቤት እየገነባ ቢሆንም መፅሀፍት ግን በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲቀርብ እያደረገ አይደለም ይህም የሚቃረን ስራ ነው ተብሏል።
በውይይቱ ላይ የተሳተፉ ደራሲያን እንዳሉት መፅሐፍት በመንግስት መደጎም እያለበት ጭራሽ እንዲጠፋ እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም አንባቢ እንዲጠፋ መንግስት ይፈልጋልን? ብለው የሚጠይቁት የውይይቱ ተሳታፊዎች ይህንንም የሚያደርገው ጠያቂ ትውልድ ስለማይፈልግ ነው ሲሉ ግምታቸውን ሰምተዋል፡፡
የዲጂታል ቴክኖሎጂ አይቀሬ ከመሆኑም በላይ ለሀገር ጠቃሚ መሆኑ አይካድም፡፡
ነገር ግን ትውልዱ መፅሐፍት ታትሞ እንዲያነብና እንዲመራመር ካልተደረገ እሮቦት የሆነ ትውልድ ለሀገር ከማፍራት አይተናነስም ሲሉ ደራሲያኑ አሳስበዋል።
አሁን ባለው የኑሮ ውድነት ምክንያትና የህትመት ዋጋ መናር ምክንያት ደራሲያን ከድርሰት ስራ ወጥተው በድለላ ስራ እየተሰማሩ መሆኑ በውይይቱ ተነስቷል።
መንግስት አንባቢ ትውልድ እንዲፈጠርና እውቀት እንደሀገር እንዲሰፋ ይህን የመፅሐፍት ተጨማሪ እሴት ታክስ ሊያነሳው ይገባል ሲል የደራሱያን ማህበሩ አሳስቧል።
በረከት አካሉ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ… https://bit.ly/33KMCqz
Comments