ታሪክን የኋሊት - አና ፍራንክ የመጨረሻውን ማስታወሻዋን ከፃፈች ዛሬ 81 ዓመት ሆነ
- sheger1021fm
- Aug 1
- 2 min read
ይሁዳዊያን በናዚ ጀርመኖች የደረሰባቸውን ፍዳ ለማሳየት አቅም አለው የሚባለውን ፅሁፍ የፃፈችው #አና_ፍራንክ የመጨረሻውን ማስታወሻዋን የፃፈችው በ1938 ዓ.ም በዛሬው ቀን ነበር፡፡
አና ፍራንክ የመጨረሻውን ማስታወሻ የፃፈችው በናዚዎች ከመያዟ 3 ቀን በፊት ነው፡፡
አና ፍራንክ የእለት ውሎዋን ማስታወሻ መፃፍ የጀመረችው 13ኛ ዓመት የልደት በዓሏን ስታከብር በተሰጣት የቀን ውሎ መፃፊያ ማስታወሻ ነው፡፡
በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታትም ከማስታወሻ በተጨማሪ በደብተር ላይ የፃፈቻቸው ማስታወሻዎች ታትመው በአለም ዙሪያ ተነባቢ ሊሆኑ በቅተዋል፡፡
አና ፍራንክ ከይሁዳውያን ወላጆቿ የተወለደችው ጀርመን ፍራንክፈርት ውስጥ ነው፡፡
ሂትለር ይሁዱዎችን ከጀርመን የማስወጣትና የማሳደድ እቅዱን ተግባራዊ ማድረግ ሲጀምር ወደ ሆላንድ ተሰደዱ፡፡
ከ2 ዓመታት በኋላ ሂትለር ሆላንድን በአራት ቀን ጦርነት ሲቆጣጠር ይሁዳውያን የጥቃት ዒላማ ሆኑ፡፡
ትምህርት ቤት እንዳይሄዱ፣ በመዝናኛ ቦታዎች እንዳይገኙ፣ ቢጫ ቀለም ያለው ኮከብ ምልክት እንዲለጥፉ ታዘዙ፡፡

ለስራ ወደ ጀመርን እንደሄዱ ጥሪ ሲተላለፍ፣ የእና እህት ማርጋሪትም ጥሪው ደረሳት፡፡
ወላጆቿ ልጃቸውን ወደ ጀርመን ለመላክ አልፈለጉም፡፡
ስለዚህ አባታቸው በሚሰራበት የንግድ ቦታ ስር በሚገኘው ምድር ቤት ለመደበቅ ወሰኑ፡፡
ከእነሱም ጋር ይሁዳዊው የንግድ ሸሪካቸው ከሚስቱና ከልጆቹ ጋር ተጨመረ፡፡
ምግብና መፃህፍት የሚያቀረቡላቸው ታማኞቻቸው ፀሐፊዎቻቸውና ሰራተኞቻቸው ነበሩ፡፡
ለ2 ዓመት ከአንድ ወር በዚያው ተደብቀው ቆዩ፡፡
አና በተደበቀችበት ምድር ቤት ሆና፣ በየእለቱ የሚያጋጥማትን “ኪቲ” ብላ በሰየመችው ማስታወሻዋ ትመዘግባለች፡፡
አብረዋት ስለነበሩት ሰዎች ባህሪ፣ ስለምትናፍቀው ነፃነትና ስለስሜቷ እየፃፈች ሁለት ዓመታት ቆየች፡፡
በባለ ቃልኪዳን ሀይሎች ድል እያገኙ የሂትለር ጦር እየተሸነፈ ባለበት ወቅት እነ አን መደበቃቸው ተጠቆመባቸው፡፡
አንና ሰባቱ ይሁዳውያን ተያዙ፡፡
አናና እህቷ ወደ ኦሽዊትዝ ካምፕ ሲወሰዱ፣ አባቷና እናቷና ሌሎቹ ወደ ሌላ ማጎሪያዎች ተላኩ፡፡
ኦሽዊትዝ በሶቪየት ጦር ነፃ ሊሆን ሁለት ወራት ሲቀሩት የ16 ዓመቷ አንና እህቷ በማጎሪያው በተስፋፋው በሽታ ሞቱ፡፡
ከስምንቱ ይሁዳውያን በሕይወቱ የተረፈው አባታቸው ፍራንክ አቶዋ ብቻ ነበር፡፡
ናዚዎች እነ አነን ይዘው ሲሄዱ፣ ፀሐፊዋ ሜፕ ጊስ ፣ በሶስት ቅፅ የተፃፉትን የአንን ማስታወሻዎች ሰብስባ አስቀመጠቻቸው፡፡
አባቷ ፍራንክ ወደሆላንድ ሲመለስ ማስታወሻዎቹን ሰጡት፡፡
ከ2 ዓመት በኋላ በደች ቋንቋ አሳተመችው፡፡
የአና ማስታወሻ ከፍተኛ ተነባቢነት ያገኘው፣ በአሜሪካ በእንግሊዝ ቋንቋ ከታተመ በኋላ ነው፡፡
“የወጣቷ ማስታወሻ” በሚል ርዕስ የታተመው መፅሐፍ ከፍተኛ ደረጃ ከተሰጣቸው መፃህፍት አንዱ ሆነ፡፡
በዓለም ዙሪያ በ70 ቋንቋዎች ታትሟል፡፡
በድራማና በፊልም በመስራቱ እውቅናውና ዝናው ከፍ ብሏል፡፡
ሐውልትም ተቀርፆላታል፡፡
አና ፍራንክ ያንን ማስታወሻ በመፃፏ “የይሁዳውያን እልቂት” ማሳያ ተደርጋ ትቆጠራለች፡፡
በኔዘርላንድስ አና ፍራንክና ቤተሰቦቿ የተደበቁበት ቦታ የቱሪስት መዳረሻ ሆኗል፡፡
አና ፍራንክ የመጨረሻውን ማስታወሻዋን ከፃፈች ዛሬ 81 ዓመት ሆነ፡፡
እሸቴ አሰፋ
ሐምሌ 25 2017
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s
Comments