top of page

ሰኔ 25 2017 - የቤት ዋጋ ንረትን ያባብሳል በሚል ትችት ሲቀርብበት የነበረው አዋጅ ጸድቋል

  • sheger1021fm
  • 6 days ago
  • 2 min read

የቤት ዋጋ ንረትን ያባብሳል በሚል ትችት ሲቀርብበት የነበረው የውጭ ሀገር ዜጎች የመኖሪያ ቤት ባለቤት የሚሆኑበትን አግባብ ለመደንገግ የወጣ አዋጅ ጸድቋል፡፡


አዋጁ አንድ የውጭ ሀገር ዜጋ 150,000 አሜሪካን ዶላር ካለው የመኖሪያ ቤት የመግዛት አልያም የመገንባት መብትን ይሰጣል፡፡


የከተማ፣ መሰረተ ልማት እና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እስካሁን ከተመሩልኝ አዋጆች ከወር ባነሰ ጊዜ ውስጥ ያጠናቀቅኩት አዋጅ ነው ብሏል፡፡


በዚህ አዋጅ መሰረት የውጭ ሀገር ዜጎች በኢትዮጵያ በየትኛውም ክልል እና ከተማ አንድ የመኖሪያ ቤት መግዛት አልያም መገንባት ይችላሉ፡፡


ረቂቅ አዋጁ እንዲጸድቅ ለምክር ቤት በቀረበበት ወቅት የምክር ቤት አባሉ ፈቲ መሃዲ(ዶ/ር) አዋጁ የተሰናዳበት ወቅት ትክክለኛ ጊዜ እንደሆነ ጠቁመው የአዋጁ መጸደቅም ለሀገሪቱ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡


አዲስ አበባ ላይ ያለውን የቤት ዋጋ እናውቃለን ያሉት የምክር ቤት አባሉ አሁን ደግሞ የውጭ ሀገር ዜጎች ሲጨመሩበት የበለጠ ዋጋውን እንዳያንረው ስጋት እንዳላቸው አስረድተዋል፡፡


አወቀ አምዛዬ(ዶ/ር) የተባሉ ሌላ የምክር ቤት አባል በበኩላቸው አዋጁን ከመርህ አንፃር እንደሚደግፉ ተናግረው የውጭ ዜጋ ቤት የመግዛት ፍላጎትን ለምን በአንድ ቤት ብቻ መገደብ አስፈለገ? ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ 

የጥያቄያቸውን መነሻ ያብራሩት አወቀ(ዶ/ር) ለምሳሌ ቤት ገዢው እንዴት ኢትዮጵያዊትን ቢያገባ እና በተወሰነ ጊዜ ልዩነት ቢለያዩ ንብረቱን እንዴት ነው የሚከፋፈሉት ሲሉ ጠይቀዋል፡፡


አበባው ደስአለው(ዶ/ር) የተባሉ ሌላ የምክር ቤት አባል ከህገ መንግስቱ ጋር ይቃረን የነበረው የአዋጁ ክፍል መሻሻሉ መልካም መሆኑን ተናግረው የሀገራችንን ዜጎች የነፍስ ወከፍ ገቢ  አላሻሻልንም በአለም አቀፍ ደረጃም ተወዳዳሪ አላደረግንም ብለዋል፡፡


በተለይ በአዲስ አበባ እና አካባቢው ዜጎች የመኖሪያ ቤት ተጠቃሚ መሆን አላስቻልንም ያሉት የምክር ቤት አባሉ እንደዚህ አይነት ውስን አቅም ባለበት ሁኔታ  የውጭ ሀገር ዜጎች በብዛት መጥተው ያሉትን መኖሪያ ቤቶች የሚገዙ እና የሚገነቡ ከሆነ ኢትዮጵያዊያን የቤት ተጠቃሚ የማይሆኑበት ሁኔታ እንዳይፈጠር ስጋት አለኝ ብለዋል፡፡


የውጭ ሀገር ዜጎች በብዛት በሚገቡ ወቅት ከፍተኛ የመግዛት አቅም ስላላቸው የግብዓቶች ዋጋ በእነዚህ አካላት እንዳይወሰን እና የኑሮ ውድነቱ እንዳይባባስ ስጋት እንዳላቸው ተናግረው ልክ በሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ዜጎች በሀገራቸው ሃብት ተጠቃሚ ሳይሆኑ ሲቀር የስርዓት አልበኝት ሊስፋፋ እንደቻለው ሁሉ በእኛም ሀገር ይህ እንዳይሆን ስጋት ስላለኝ አዋጁን ለመገደፍ እቸገራለው ብለዋል፡፡


ለጥያቄዎቹ ምላሽ የሰጡት የከተማ፣ መሰረተ ልማት እና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ እሽቱ ተመሰገን(ዶ/ር) ይህ አዋጅ ከተመራላቸው ወር እንዳማይሞላው ተናግረው  በዚህ አራት ዓመት ቆይታዬ እንደዚህ ዓመት ብዙ አዋጅ በፍጥነትም በብዛትም ያጸደቅንበትን ጊዜ የለም ብለዋል፡፡


በአዋጁ ላይ በቂ ወይይት መደረጉን የተናገሩት ምክትል ሰብሳቢው ከሁሉም አዋጆች ግን ይህ አዋጅ በፍጥነት ተዘጋጅቷል ሲሉ ተናግረዋል፡፡


ምክትል ሰብሳቢው አዋጁ የውጭ ዜጎች አንድ ቤት ምናልባት እስከ ባለ አንድ ፎቅ እንዲገንቡ ነው እንጂ ከዚያ በላይ እንዲገነቡ አዋጁ እንዳማይፈቅድ ተናገረው ይህ መሆኑ ደግሞ ለሀገሪቱ የውጭ ምንዛሪ እና የስራ እድል ይፈጥራል ሲሉ አስረድተዋል፡፡


የሊዝ መብትን በተመለከተ ለቀረበው ጥያቄም ምክትል ሰብሳቢው በሰጡት ምላሽ የውርስ ህጉ ልክ ለኢትዮጵያዊን እንደሚሰራው ሁሉ ለውጭ ዜጎችም ይሰራል ብለዋል፡፡


የኢትዮጵዊያንን እድል ይገፋል የሚለው ስጋት አግባብ እንደሌላው የተናገሩት ምክትል ሰብሳቢው እንዲያውም አዋጁ ገዢ ላጡ ሪል ስቴት አልሚዎች የገበያ እድል ነው የሚፈጥረው ሲሉ መልሰዋል፡፡


የቋሚ ኮሚቴው ዋና ሰብሳቢ መሃመድ አብዶ(ዶ/ር) አዋጁ ተለዋዋጭ መሆን የሚችል ስለሆነ የሚቀርቡ የቤት ፍላጎቶችን አይተን እንደየአስፈላጊነቱ የቤት መጠንን ከፍ ማድረግ ያስችለናል ብለዋል፡፡


አዋጁ የዋጋ ንረቱን የሚያባብስ ሳይሆን የሚጠቅም እንደሆነ ተናግረው  አዋጁ ከውጭ ለሚመጣ ገንዘብ በር ከፋች ስለሆነ እንዲጸድቅ ጠይቀዋል፡፡ ምክር ቤቱም አዋጁን በአብላጫ ድምጽ አጽድቆታል፡፡


ያሬድ እንዳሻው


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…





Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page