ሰኔ 21 2017 - ብሔራዊ ባንክ አንዳንዴ ሊከስር ሌላ ጊዜ ደግሞ ከልክ በላይ ሊያተርፍ ይችላል ሲሉ የባንኩ ገዢ ተናገሩ
- sheger1021fm
- 8 minutes ago
- 2 min read
የባንኩ ገዢ ይህን የተናገሩት፤ በህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ቀርበው ለፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ዓመታዊ ሪፖርታቸውን ባቀረቡበት ወቅት ነው፡፡
ቋሚ ኮሚቴው፤ ብሔራዊ ባንክ በምንዛሪ ተመን ለውጥ ምክንያት ኪሳራ እንደገጠመው ተናግሮ፤ ባንኩን ከኪሳራ በማውጣት ዘላቂ እና የተረጋጋ የፋይናንስ አቅም እንዲፈጥር የተቀመጠው ስትራቴጂ ምን እንደሆነ ጠይቋል፡፡
የባንኩ ገዢ በሰጡት ምላሽም በሔራዊ ባንክ ለትርፍ የተቋቋመ ተቋም እንዳልሆነ መረዳት እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል፡፡
«በሔራዊ ባንክ የትርፍ መስሪያ ቤት አይደለም ያሉት አቶ ማሞ ኪሳራ ሲባል ሰው መጀመሪያ የሚመጣለት ልክ እንደትርፍ የተቋቋመ መስሪያ ቤት እቃ ሽጦ ወይም አገልግሎት ሰጥቶ እያተረፈ የሚኖር መስሪያ ቤት መስሎ ይሰማቸዋል ግን ይሄ አይደለም » ብለዋል፡፡

ብሔራዊ ባንክ የተቋቋመው የዋጋ ንረት መረጋገትን ለመፍጠር እና የፋይናንስ ዘርፉን የተረጋጋ ለማድረግ ነው ያሉት ገዢው ብሔራዊ ባንክ ከሰረ የሚባል ነገር የለም፤ ይሄ የሁሉም ሀገራት የማዕከላዊ ባንኮች አሰራር ነው ብለዋል፡፡
ብሔራዊ ባንክ ዘንድሮ አበድሮ ያልተመለሰለት ገንዘብ ስላለ ኪሳራ ድርሶበታል የሚባለው ወሽት ነው ብለዋል አቶ ማሞ ምህረቱ፡፡
ባንኩ ለመንግስት አልያም ለግል ባንኮች አበድሮ ያልተከፈለው ገንዘብ እንደሌላ የተናገሩት ገዢው “እስካሁን ያበደርነው ከነወለዱ በትክክል ተመልሷል” ሲሉ አስረድተዋል፡፡
እውነቱ ብሔራዊ ባንክ በሰራው ስራ የኦፕሬሽናል ትርፍ (operational profit) 27.6 ቢሊዮን ብር እንደሆነ ያስረዱት አቶ ማሞ ብሄራዊ ባንክ አንዳንዴ እየከሰረም ቢሆን ኢኮኖሚውን ሊያረጋጋ ይችላል ብለዋል፡፡
ለማሳያም ባንኩ ከሌሎች ባንኮች ገንዘብ በሚውስድበት ጊዜ ተለቅ ያለ ወልድ ይከፍላል፤ ወለዱ ከፍ ባለ ቁጥር ደግሞ የባንኩን ባላንስ ሺት (balance sheet) ይነካል፤ ስለዚህ በሔራዊ ባንክ የዋጋ መረጋገት አለማን ለማሳካት ባንኩ አንዳንዴ ከስሮ ሌላ ስራ ሊሰራ ይችላል፤ ይሄም በማዕከላዊ ባንክ አሰራር የተለመድ እና ሚጠበቅ ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡
ለማሳያም ያለፉትን ሶስት ዓመታት የማዕከላዊ ባንኮችን ፋይናንሻል ሪፖርት ብንመለከት የአሜሪካ የማዕከላዊ ባንክ፣ የአውሮፓ ማዕከላዊ ባንክ፣ የእንግሊዝ ባንክ እና የኬንያን ማዕከላዊ ባንክ ሁሉም ሞኒታሪ ኦፕሬሽንስ (Monetary Operations) በሚሰሩበት ወቅት ኪሳራ ገጥሟቸዋል ብለዋል፡፡
ልክ ለትርፍ እንደተቋቋመ የአምራች ኩባንያ ብሄራዊ ባንክ አተረፈ ከሰረ መባል እንደሌለበት አቶ ማሞ በምክር ቤት ቆይታቸው አስረድተዋል፡፡
ያሬድ እንዳሻው
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s
📌 Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
Comments