ሚያዝያ 8 2017 - የሙስሊም ሴቶች የትምህርት ቤት አለባባስ ጉዳይ ግልፅ የሆነ መፍትሄ እንዲሰጠው በፓርላማ አባላት ተጠየቀ
- sheger1021fm
- Apr 16
- 2 min read
የሙስሊም ሴቶች የትምህርት ቤት አለባባስ ጉዳይ ግልፅ የሆነ መፍትሄ እንዲሰጠው በፓርላማ አባላት ተጠየቀ፡፡
የትምህርት ሚኒስቴር በበኩሉ በትምህርት ቤት ኒቃብ ለብሶ መገኘት ፖሊሲው አይፈቅድም ብሏል፡፡
''የሙስሊም ሴት ተማሪዎች አለባበስ ጉዳይ መፍትሔ እስካላገኘ ድረስ እኛ መጠየቅ አይሰለቸን እናንተ ጥያቄው አይሰላቻችሁም ወይ?'' ሲሉ የምክር ቤት አባሉ፤ የትምህርት ሚኒስቴርን ጠየቁ፡፡
''የኢትዮጵያ ህግ እና ደንቦች በዚህ ጉዳይ ላይ የወጡ ሂጃብ ለብሶ ትምህርት መማርን የሚከለክሉ አይደሉም፤ ኒቃብ ግን አይፈቀድም'' ብለዋል ትምህርት ሚኒስቴር ብርሀኑ ነጋ (ፕ/ር)፡፡
መንግስት በህገ መንግስት ላይ በተቀበላቸው በአለም አቀፍ ስምምነቶችም ፍትሃዊ እና አካታች ትምህርት ለሁሉም ዜጎች የማቅረብ ግዴታ እንዳለበት የጠቆሙት የምክር ቤት አባሉ ኡስታዝ ካሚል ሸምሱ፤ ''ባለፈው በምክር ቤቱ የወጣው የአጠቃላይ ትምህርትም አዋጅም አንቀጽ 8 ላይ በግልጽ የተቀመጠው ትምህርት ከማንኛውም አድልኦ አሰራር የፀዳ መሆን እንዳለበት በግልጽ የደነገገ ነው'' ብለዋል፡፡

“ይህም ሲተነትን ደግሞ ብሄርን፣ በሃይማኖትን፣ ጾታን፣ እድሜን፣ አካል ጉዳተኞችን ወዘተ መሰረት ያደረገ ምንም ዓይነት ልዩነት መኖር የለበትም ይላል” ብለዋል፡፡
''በአሁኑ ሰዓት ግን በተለያዩ ቦታዎች የትምህርት ዘርፉም ሆነ በሀገሪቱ ብዙ አጀንዳ እያሉ ለምንድነው የአለባበስ ጉዳይ አጀንዳ የሚሆነው?'' ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
''ሙስሊም ሴት እኮ ሂጃብ ስትለብስ፣ ኒቃብ ስትለብስ የምትሸፍነው ጸጉሯን እንጂ የውስጥ አይምሯዋን አይደለም'' ያሉት የምክር ቤት አባሉ ኡስታዝ ካሚል ሸምሱ ለማሳያም ባለፈው ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ 3.87 ውጤት ያመጣቸውን ሴት ተማሪ አንስተዋል፡፡
''አስተማሪዎችም፣ ተማሪዎችም ሃይማኖት አላቸው ስርዓቱ ነው ሴኩላር የሙስሊም፣ የኦርቶዶክስ ወይም የክርስትና እምነት በስርዓተ ትምህርት ውስጥ አይካተትም ማለት እና ተማሪዎችን ሃይማኖታችሁን ተው ማለት ሁለቱ ለየቅል ናቸው'' ብለዋል፡፡
''በአለባበስ ላይ የሚነሱ ጉዳዮች ግልጽ መፍትሄ ማግኝት አለባቸው'' ያሉት የምክር ቤት አባሉ ''እኛ ጭቆናው እስካልቆመ ድረስ ጥያቄ መጠየቅ እንቀጥላለን፤ እናንተ ግን ጥያቄው እራሱ አይሰለቻችሁም ወይ? ለአንዴ እና ለመጭረሻ ጊዜ ለምን ይሄ ነገር ግልጽ የሆነ አቅጣጫ አይሰጥበትም ብለዋል።
''ሴት ተማሪዎች ኒቃባቸውና ሂጃባቸውን ለብሰው ሲገቡ የደህንነት ጉዳይ ይነሳል፤ ሴት ፈታሾች ወይም ጠባቂዎች አስፈላጊ ቦታ ላይ ያንን ማድረግ ይቻላል ለምንድነው ሰፋ አድርገን ማየት ያልተቻለው?'' ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
ለጥያቄው ምለሽ የሰጡት የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ(ፕ/ር) በበኩላቸው ''የኢትዮጵያ ህግ እና ደንቦች በዚህ ጉዳይ ሂጃብ ለብሶ ትምህርት መማርን የሚከለክሉ አይደሉም፤ ኒቃብ ግን አይፈቀድም'' ብለዋል፡፡
''ማንም ሂጃብ ለበሰ ተብሎ ከትምህርት ቤት መከልከል የለበትም'' ያሉት የትምህርት ሚኒስትሩ ''ኒቃብ ግን ከዚህ ይለያል'' ብለዋል፡፡
''ህፃናት፣ ልጆች ባሉበት ትምህርት ቤት አንድ ሰው ፊቱን ተሸፍኖ በሚገባ ጊዜ የደህንነት ስጋት አለ'' ሲሉ ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ ተናግረዋል፡፡
ያሬድ እንዳሻው
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://tinyurl.com/ky57kspd
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s
📌 Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
📌 Linkedin : https://tinyurl.com/yhycs5r
📌Spotify : https://shorturl.at/QG8f2
Comments