top of page

መስከረም 21፣2017 - የግንባታ ፈቃድ እና ቁጥጥር ባለስልጣን ለሁሉም ክፍለ ከተሞች ብሎ ያስተላለፈው ደብዳቤ ማነጋገሩን ቀጥሏል

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የግንባታ ፈቃድ እና ቁጥጥር ባለስልጣን ከ15 ቀናት በፊት ለሁሉም ክፍለ ከተሞች ብሎ ያስተላለፈው ደብዳቤ ግርታም፣ የግንባታ መቀዛቀዝም፣ በምንድነው ነገርነቱም ማነጋገሩን ቀጥሏል፡፡


ደብዳቤው ህንፃ ከመንገድ መራቅ ያለባቸውን ርቀት (setback)፣ የመሬት ስፋት ዝቅተኛ ገደብ እና የህንፃ የጎን ስፋት የሚመለከት ነው፡፡


በዚህም ህንፃ ከመንገድ መራቅ ያለባቸው 10፣ 5፣ 3 እና 2 ሜትር እንዲጠበቅ፣ በ15 ሜትር እና በላይ ስፋት ያላቸው መንገዶች የሚያዋስኗቸው ይዞታዎች ዝቅተኛው የቦታ ስፋት(setback) ከተቀነሰ በኋላ ቢያንስ 500 ሜትር መሆኑ መረጋገጥ እንዳለበት እንዲሁም ዝቅተኛው የህንፃ የጎን ስፋት በ20 ሜትር ያላነሰ መሆን እንደሚገባው ያስረዳል፡፡


እነዚህም የኮሪደር ልማት በሚተገበርባቸው ሆነ በኮሪደር ልማት ክልል ውጪ ጭምር በከተማ አስተዳደር ወሰን ውስጥ በሙሉ ተፈፃሚ እንደሚሆንም በደብዳቤው ተጠቅሷል፡፡


የግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን ይህ ጉዳይ ሰኔ 2016 ዓ.ም በከተማ ካቢኔ የፀደቀ መሆኑንን ጠቅሷል፡፡


ሆኖም ውሳኔው ተግባራዊ እንዲደረግ በሰርኩላር ቢተላለፍም በየደረጃው ያሉ አመራሮች እና ባለሞያዎች ህጉን እያጣሱት መሆኑን ባለስልጣን መ/ቤቱ ተናግሯል፡፡


ይህ ክፍለ ከተሞች በጥብቅ እንዲያስፈፅሙት የተላለፈላቸው የአተገባበር መመሪያ ግን ግርታን ፈጥሯል፡፡


ግንባታም በከፊል እንዲቆም አስገድዷል።


አርክቴክት ዮሐንስ መኮንን ህንፃ ከመንገድ መራቅ ያለበት በሚል የተጠቀሰው 10፣ 5፣ 3 እና 2 ሜትር ከከተማዋ መሪ እቅድ ወይንም ማስተር ፕላን ላይ የሌለ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡


ማስተር ፕላኑ ላይ የተጠቀሰው 2፣ 3 እና 5 መሆኑ ጠቅሰው 10 ሜትር የሚለው እንደሌለ አንስተዋል።


በተለይ በሶስት በኩል መንገድ የሚያዋስናቸው ላይ የተጀመሩ ግንባታዎች በዚሁ የተነሳ መቆማቸውን ጠቅሰዋል።


ቀደም ባለው ገዜ አልሚዎች ይዞታቸው በሁለት በሶስት በኩል መንገድ ሲያዋስነው በተለይ ለንግድ ስራዎች አመቺ ስለሚሆን እንደ እድል ነበር የሚቆጥሩት አሁን ግን እንደ ክፋ እድል ያዩታል ብለዋል።


ሌላው ጥብቅ ክትትል እና ቁጥጥር እንዲደረግበት በሚል የተከማዋ የግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን የጠቀሰው በ15 ሜትር እና በላይ ስፋት ያላቸው መንገዶች የሚያዋስኗቸው ይዞታዎች የቦታ ስፋት ከመንገድ መራቅ ያለባቸው 10፣ 5፣ 3፣ 2 ሜትርም ከተቀነሰ በኋላ የቦታው ስፋት 500 ሜትር ካሬ መሆኑን ማረጋገጥ የሚለው ነው።


በሌላ አነጋገር ከ500 ካ.ሜ ስፋት በታች ለሆነ ይዞታ የግንባታ ፈቃድ አይሰጥም፡፡


አርክቴክት ዮሐንስ ይህን በተመለከተም ሲያስረዱ በአዋጅ ደረጃ ካለው የንብረት አዋጅ አብሮ የሚሄድ አይደለም ብለዋል።


የከተማዋ ማስተር ፕላን በአዋጅ የተቋቋመ ቢሮ መሆኑን የሚያስረዱት ባለሞያው አዋጁ ተትቶም ከሆነ በአዋጅ መሆን አለበት አለበለዚያ እሱን የሚጥስ ህግ የሚወጣ ከሆነ ትክክል አይደለም ብለዋል፡፡


የግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን በደብደቤ ላይ አንዳንድ ሲል የጠቀሳቸው አልሚዎች የካቢኔውን ውሳኔ በመተላለፍ አስፈላጊው የዲዛይን ማሻሻያ ሳያደርጉ እና የግንባታ እርከን ማሳወቂያ ሳይወስዱ ስነ ምግባር ከጎደላቸው አመራሮች ጋር በመመሳጠር ግንባታ ለማድረግ ጥረት አድርገዋል ብሏል፡፡


አርክቴክት ዮሀንስ እንደሚሉት ይህ የመጣው ግልፅነት በመታጣቱ ነው ይላሉ፡፡


የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን በምክትል የቢሮ ሀላፊው ዳዊት ሁንዴሣ ተፈርሞ መስከረም 3/2017 ዓ.ም ስለወጣውና የሴትባክ ህግ አተገባበርን ይመለከታል በሚል ስለጠቀሰው ደብዳቤ ምን ያስረዳል?


ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 ሀላፊዎች ለማነጋገር ያደረገው ሙከራ ለጊዜው አልተሳካም፡፡

ንጋቱ ሙሉ

Comments


bottom of page