top of page

ሐምሌ 17፣ 2016 - በአዲስ አበባ በቅርቡ ስራ በጀመረው የኮሪደር ልማት አካባቢ ደንብ ተላልፈው አቆሽሸዋል የተባሉ ተቋማት በድምሩ 340,000 ብር ተቀጡ

በአዲስ አበባ በቅርቡ ስራ በጀመረው የኮሪደር ልማት አካባቢ ደንብ ተላልፈው አቆሽሸዋል የተባሉ ተቋማት በድምሩ 340,000 ብር ተቀጡ፡፡

 

በዚሁ ጉዳይ በአግባቡ ሀላፊነታቸው አልተወጡም የተባሉ ደንብ አስከባሪዎችም ከስራ ታግደዋል፡፡

 

በቅርቡ ግንባታቸው ተጠናቆ ለህዝብ ክፍት በተደረጉት የልማት ኮሪደሮች በሁለት ቀን ብቻ በተደረገ ቁጥጥር ነው የ340,000 ብር ቅጣት የተጣለው ተብሏል፡፡

 

መረጃውን ያገኘነው ከከተማ አስተዳደሩ የደንብ ማስከበር ባለስልጣን ሲሆን እስካሁን ከፍተኛውን ቅጣት የጣለው የካ ክፍለ ከተማ ሲሆን በ4 የመንግስት ተቋማት ላይ በድምሩ 220,000 ብር ቅጣት ጥሎባቸዋል፡፡

 

ከመካከላቸው ከፍተኛውን 100,000 ብር ቅጣት የተቀጣው የኢትዮጵያ ብዝሃ ሕይወት ኢንስቲትዩት ሲሆን የተቀጣበት ምክንያት ተቋሙ ከቅጥር ግቢው ውጭ እስከ 5 ሜትር ርቀት ደረሰ ያለውን ቦታ በአግባቡ አላፀዳም ተብሎ ነው፡፡

 

በሌላ በኩል የመንግስት የልማት ድርጅት የሆነው የኢንዱስትሪ ፓርኮች ኮርፖሬሽን 50,000 ብር የተቀጣው ደንብ ተላልፎ የድርጅቱ ሰራተኞች የተጠቀሙባቸውን የተለያዩ አገልግሎት የሰጡ ወረቀቶችን ሲያቃጥል ተይዞ መሆኑን ሰምተናል፡፡

 

የአዲስ አበባ ካቢኔ አሻሽሎ ባወጣው የቅጣት ተመን መሰረት ተግባራዊ በተደረገው ደንብ የከተማ አስተዳደሩ አካባቢን እንዲያፀዱ ያደራጃቸው የፅዳት አገልግሎት ሰጭ ማህበራትም ከቅጣት አላመለጡም፡፡

ከየካ ገስት ሐውስ እና አካባቢው ቆሻሸን በመኪና ገብተው መጫን ሲገባቸው የልማት ኮሪደሩን በማቆሸሽና በማዝረክረክ በሚል ሰለሞን እና ቻላቸው የፅዳት ማህበር 20,000 ብር ተቀጥቷል፡፡

 

የካ ገስት ሐውስ ደግሞ 50,000 ሺህ ብር ቅጣት ተጥሎበታል ተብሏል፡፡

 

በሌላ በኩል አራዳ ክፍለ ከተማ በ1 ቀን ባደረገው የቁጥጥር ስራ የቆሻሻ አያያዝን በተመለከተ ደንብ ተላልፈዋል ያላቸውን 3 ተቋማትን በድምሩ 120,000 ሺህ ብር ቀጥቷቸዋል፡፡

 

ከመካከላቸው ኦላ ኢነርጂ የነዳጅ ማደያ ያመነጨውን ቆሻሻ በአግባቡ አላስወገደም ተብሎ 50,000 ብር ተቀጥቷል፡፡

 

በፍቅር ባርና ሬስቶራንት ደግሞ የአጥትና የስጋ ተረፈ ምርትን ባልተፈቀደ ቦታ በመጣል 50,000 ብር እንዲሁም ይደምቃል ወርቅነሽ እና ጓደኞቿ የተባለ የፅዳት አገልግሎት ስም ማህበር ለቆሻሻ ማቆያ ወይም ማስወገጃነት ከተፈቀደ ቦታ ውጭ ቆሻሻን በመጣል 20,000 ብር ተቀጥቷል፡፡

 

በተያያዘ የየካ ክፍለ ከተማ ደንብ ፅ/ቤት ደንብ ሊያስከብሩ ስምሪት ተሰጥቷቸው በአካባቢው እያሉ ሀላፊነታቸውን ባለመወጣት የኮሪደር ልማቱ እንዲቆሽሽ ምክንያት ሆነዋል ያላቸውን 2 ደንብ አስከባሪዎችን ከስራ ማገዱንም ሰምተናል፡፡

 

ከኮሪደር ልማቱ በኋላ የከተማ አስተዳደሩ ካቢኔ የቆሻሻ አያያዝ ላይ በሚፈጠር የደንብ መተላለፍ ሲጣል የቆየው ቅጣት አስተማሪ አይደለም በሚል ማሻሻያ አድርጎበታል፡፡

 

ተሻሽሎ ስራ ላይ በዋለው ደንብ መሰረትም ቅጣቱ ከፍተኛው 100,000 ሺህ ዝቅተኛ 2,000 ብር ሆኗል፡፡

 

የድርጅትን ወይም ተቋምን እስከ በ5 ሜትር ርቀት ድረስ አለማፅዳት እና ከፅዳት አስተዳደር ኤጀንሲ ፈቃድ ውጭ ደረቅ ቆሻሻን ወደ ከተማዋ ክልል ያስገባ ወይም ያስወጣ 100,000 ብር ቅጣት እንደሚጠብቃቸው ደንቡ ላይ ሰፍሯል፡፡

 

በዚህም መሰረት መኪና ውስጥ ሆኖ በመስኮት ማንኛውም ዓይነት ቆሻሻ ወደ ውጭ የወረወረ፣ እንዲሁም እግረኛም ቢሆን በመንገድ ላይ የሲጋራ ቁራጭ፣ የሶፍት ወረቀት፣ ፌስታል፣ የጫት ገለባ፣ የፍራፍሬ ተረፈ ምርት፣ የማስቲካ ወረቀት መሰል ቆሻሻ ሲጥል ከተገኘ 2,000 ብር ያስቀጣል፡፡

 

ደረቅ ቆሻሻን ከጊቢው አውጥቶ ባልተረፈቀደ ቦታ የጣለ ደግሞ የመኖሪያ ቤት ከሆነ 2,000 ከኢንዱስትሪ ከሆነ 50,000 ብር እና ለጤና ተቋም ከሆነ 30,000 እንዲሁም እና የተጣለው ደረቅ ቆሻሻ የመነጨው ከተጠቀሱት ውጭ በሆኑ ከሌሎች ድርጅት ከሆነ 10,000 ብር እንደሚያስቀጣ የአዲስ አበባ ካቢኔ አሻሽሎ ካፀደቀው ደንብ ላይ ተመልክተናል፡፡

 

ትዕግስት ዘሪሁን


 

 

Comentarios


bottom of page