በመንግሥት እና ራሱን የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት ብሎ ከሚጠራው ታጣቂ ቡድን ጋር በሁለት ዙር ሲካሄድ የነበረው ንግግር ያለ ውጤት ተቋጭቷል ተባለ።
ይህን ያለው የመንግሰት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ነው።
መንግስት "ሸኔ" እያለ ከሚጠራው ታጣቂ ቡድን ጋር በታንዛንያ ዛንዚባር ከወራት በፊት ውይይት ተካሂዶ ሳይቋጭ መቅረቱን አስታውሷል።
በዚያ የውይይት ወቅት ቡድኑ ከ60 ዓመታት በፊት የኦሮሞም የሌሎች የኢትዮጵያ ብሔረሰቦችም ሁሉ ጥያቄዎች የነበሩና ተመልሰው ያደሩ ጥያቄዎችን አንስቷል ሲል አገልገሎቱ ጠቅሷል።
በተለይም ከለውጥ በኋላ በስራ ላይ የዋሉ ጉዳዮችን ከመጥቀስ ውጭ የሚቆጠርና የሚቋጠር አጀንዳ ማምጣት ባለመቻሉ በመንግሥት በኩል በስከነትና በማግባባት ላይ ብቻ ታጥሮ በቀጠሮ ተንጠልጥሎ እንዲቆይ ማድረጉ ተመራጭ አካሄድ ነበር ሲል የመንግስት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት አስረድቷል።
ባለፉት 2 ሳምንታትም ሁለተኛ ዙር ውይይት ታንዛንያ ዳሬ ሰላም ላይ ሲካሄድ ቆይቷል ብሏል።
ታጣቂ ቡድኑ በዚህኛው ዙርም "መንግሥት አዝሎ መንግሥት ያድርገኝ ከሚል አጉራ ዘለልነት ያለፈ የድርደር ነጥብ ማምጣት አልቻለም" ሲል የአገልግሎቱ መግለጫ አስረድቷል።
በመንግውት በኩል በሀገሪቱ ሰላም ሰፍኖ ኢትዮጵያ ያሉዋትን ጸጋዎች ወደ ተጨባጭ ሀብትና አቅም ቀይራ ብልጽግናዋን ታረጋግጥ ዘንድ ካለው ጉጉት በመነጨ ከግማሽ መንገድ በላይ ተጉዞ ለጉዳዩ እልባት ለመስጠት ሞክሯል ተብሏል።
ነገር ግን ውይይቱ ያለ ውጤት ተበትኗል ሲል መግለጫው አስረድቷል።
መንግሥት ለሰላማዊ መፍትሔ ያለው አቋም እንደተጠበቀ ነው ያለው መግለጫው ሕግና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን የማስከበር ተልዕኮውን አጠናክሮ ይቀጥላል ብሏል።
በዋና የጦር አዛዦቹ ድርድር የተቀመጠው ታጣቂ ቡድኑ ለድርድሩ ያለ ውጤት መጠናቀቅ መንግስትን ተጠያቂ አድረጓል፡፡።
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ… https://bit.ly/33KMCqz
Comments