top of page

ግንቦት 26 2017 - ከዚህ ቀደም በተርሚናል አገልግሎት ተሰማርተው ሲሰሩ የቆዩ ወደ ሌላ የስራ ዘርፍ በመሰማራት ድጋፍ እንደሚያደርግ የአዲስ አበባ ሥራና ክህሎት ቢሮ ተናገረ

  • sheger1021fm
  • Jun 3
  • 2 min read

በአዲስ አበባ ከዚህ ቀደም በትራንስፖርት የተርሚናል አገልግሎት ተሰማርተው ሲሰሩ የቆዩ ዜጎች አሰራሩ በሚፈቅደው መሰረት ወደ ሌላ የስራ ዘርፍ በመሰማራት እንዲሰሩ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ የአዲስ አበባ ሥራና ክህሎት ቢሮ ተናገረ፡፡


በከተማዋ በትራንስፖርት ስራ አስከባሪነት ሲሰሩ የነበሩ ማህበራት በአዲስ እንደሚቀየሩ የከተማ አስተዳደሩ ተናገሮ ነበር፡፡


በዚህም ቢሮው በተርሚናል አገልግሎት የተደራጁ አዳዲስ ኢንተርፕራይዞች /ተራ አስከባሪ ማህበራት/ የስራ ማስጀመሪያ መርሀ ግብር ዛሬ በአድዋ መታሰቢያ ሙዚየም አካሂዷል።


በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ሥራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጥራቱ በየነ የከተማ አስተዳደሩ በዘርፉ ያለውን ብልሹ አሰራር በመቅረፍና ዘመናዊ የአገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓት ለመዘርጋት ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የተለያዩ ተቋማት ጋር በመሆን ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል አዳዲስ የተርሚናል ኢንተርፕራይዞች እንዲደራጁ አድርጓል ብለዋል።


የከተማ አስተዳደሩ የትራንስፖርት አገልግሎቱን ለማቀላጠፍ የዜጎችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በቴክኖሎጂ የተደገፈ እና በሰለጠነ የሰው ሀይል እንዲመራ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱንም ተናግረዋል።


በዚህም ዘርፉ የሚመራበት መመሪያ በማዘጋጀትና በሰለጠነ የሰው ሀይል እንዲመራና የዜጎችን እንግልትና እሮሮ ለመቅረፍ 996 ዜጎች በ87 ኢንተርፕራይዞች ተደራጅተዋል ተብሏል፡፡


ቢሮው ከዚህ ቀደም በዘርፉ ተሰማርተው ሲሰሩ ለቆዩ ዜጎች ምስጋና ያቀረበ ሲሆን አሰራሩ በሚፈቅደው መሰረት ወደ ሌላ የስራ ዘርፍ በመሰማራት ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ሲሉ አቶ ጥራቱ በየነ ተናግረዋል።


የተርሚናል አገልግሎቱን የተሻለ ለማድረግና ዘርፉ ለዜጎች የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ እንዲጨምር የትራንስፓርት አገልግሎት መመሪያ በማሰናዳት ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ከስራና ክህሎት ቢሮ ጋር በጋራ በመስራቱ የሰለጠነ የሰው ሀይል ስምሪት መስጠቱ በትራንስፖርት የተርሚናል አገልግሎቱን ብልሹ አሰራር ለመቅረፍ አስችሏል ሲሉ የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊው አቶ ያብባል አዲስ ተናግረዋል።


የአዲስ አበባ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ በበኩላቸው የትራንስፖርት ተርሚናል በርካታ ህዝብ አገልግሎት የሚያገኝበት በመሆኑ ዜጎች ለ አላስፈላጊ ወከባና እንግልት እንዲሁም ለወንጀል እንዳይጋለጡ በስራው ላይ የሚሰማሩ ዜጎች ከፀጥታ አካላት ጋር መስራት እንደሚገባቸው አሳስበዋል።


የአዲስ አበባ ሥራና ክህሎት ቢሮ ከትራንስፖርት ቢሮ እና ከሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ጋር በመሆን በዘርፉ ለሚሰማሩ ባለሙያዎች በስድስቱ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጆች በክህሎት፤ በስራ አካባቢ ጸጥታ እና ደህንነት እንዲሁም የትራንስፖርት አገልግሎት ዘርፍ አሰራር ላይ ስልጠናዎች ሰጥቷል ተብሏል።


ምህረት ስዩም


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…





Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page