ግንቦት 19 2017 - ከተሻሻለ ከ20 ዓመት በላይ ሆኖታል የተባለው የኢትዮጵያ የውሃና ኢነርጂ ፖሊሲ በአዲስ ሊተካ ዝግጅት እየተደረገ ነው።
- sheger1021fm
- 1 day ago
- 1 min read
ጊዜው የሚጠይቀውን ጥያቄ የመመለስ አቅም አንሶታል፣ ከተሻሻለም ከ20 ዓመት በላይ ሆኖታል የተባለው የኢትዮጵያ የውሃና ኢነርጂ ፖሊሲ በአዲስ ሊተካ ዝግጅት እየተደረገ ነው።
አሁን በስራ ላይ ያለው የኢትዮጵያ #የውሃ_ፖሊሲ በ1992 የኢነርጂ ፖሊሲው ደግሞ በ1986 የወጣ ነው።
ይህ ከ20 ዓመት በላይ ሳይሻሻል መቆየቱ ፖሊሲው ወቅቱ የሚጠይቀውን ጥያቄ የመመለስ አቅም እንዳይኖረው አድርጎታል ተብሏል።
ኢትዮጵያ ካሏት 12 ተፋሰሶች 8ቱ ድንበር ተሻጋሪ መሆናቸውን ያነሱት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ሀብታሙ ኢተፋ(ዶ/ር) ለኢትዮጵያ የውሃ ነገር ከመጠጥና የሃይል ምንጭነት ባለፈ የዲፕሎማሲ፣ የፀጥታና ቀጠናዊም ጉዳይ ነው ብለዋል።
ይህንን ሊመጥን የሚችል የጊዜውን ጥያቄ የሚመልስ ፖሊስ ማሰናዳትም የግድ አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል።
አሁን በስራ ላይ ያለው ፖሊሲ የድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን አጠቃቀም፣ የግድብ ደህንነትን በተመለከተና መሰል የውሃ አስተዳደር ጥያቄዎችን የመመለስ ክፍተት ያለበትና ነጥቦቹን በዝርዝር ያላፍታታ ነው ተብሏል።

የኢነርጂ ፖሊሲውም የግሉ ዘርፍ እንዲሳተፍ ያልተካተቱ ሌሎች ዝርዝር ጉዳዮችንም እንዲይዝ ተደርጎ ረቂቅ ፖሊሲው መሰናዳቱን አብራርተዋል።
የፖሊሲ ረቂቁ ትናንት የተወካዮች ምክር ቤት የውሃ መስኖና አየር ንብረት ቋሚ ኮሚቴ እንዲሁም ጉዳዩ ይመለከታቸዋል የተባሉ ተቋማት ተወካዮች በተገኙበት ቀርቦ ተጨማሪ የማዳበሪያ ሀሳብ ተዋጥቶበታል።
ረቂቅ ፖሊሲው የሚጨመሩ ሀሳቦች ታክለውበት ወደ ሚኒስትሮች ምክር ቤት ይላካል ተብሏል።ቴዎድሮስ ወርቁ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s
📌 Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
📌 Linkedin : https://shorturl.at/21bFN