ግንቦት 18 2017 - ከድህነት ወለል በታች የሆነ ህይወት የሚገፉ ሰዎች በኢትዮጵያ
- sheger1021fm
- May 26
- 2 min read
በኢትዮጵያ ከሃያ ዓመት በፊት ከድህነት ወለል በታች የሆነ ህይወት የሚገፉ ሰዎች ከአጠቃላይ ህዝቡ እስከ 48 በመቶ ድርሻ እንደነበራቸው ይነገራል።
በብዙ ጥረት ይህን ቁጥር በፈረንጆቹ 2015 ላይ እስከ 19 በመቶ ዝቅ ማድረግ እንደተቻለ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ከድህነት ወለል በታች የሆነ ኑሮ የሚገፉ ሰዎች ብዛት ዳግም እያሻቀበ እንደሚገኝ ተሰምቷል።
ድርሻው አሁን ላይ ወደ 24 በመቶ ማደጉን በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ባለሞያዎች ማህበር ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ሞላ አለማየሁ ነግረውናል።
ከድህነት ወለል በታች የሆነ ኑሮ የሚገፉ ሰዎች ቁጥር የጨመረበት አንዱ ምክንያት የሚተገበሩ ፖሊሲዎች ናቸው ተብሏል።
ዶክተር ሞላ እንደሚናገሩት በመንግስት ስራ ላይ የሚውሉ ፖሊሲዎች ሰዎችን ከድህነት ኑሮ ማላቀቅ አልቻሉም።
በርግጥ መንግስት ይህን ያህል ቁጥር ያለውን ህዝብ ከድህነት አላቅቃለሁ፤ ለዚህን ያህሉ ደግሞ የምግብ ዋስትናቸውን አረጋግጣለሁ ብሎ ፖሊሲዎቹን እንደሚያወጣና ስራ ላይ እንደሚያውል ጠቅሰዋል።
ውጤቱ ግን እንደተባለው ሆኖ እንዳልተገኘ በማህበራቸው በተደረገ ጥናት መረጋገጡን ነግረውናል።
ለአብነትም በፈረንጆቹ 2018 ላይ በመንግስት የተተገበሩ ፖሊሲዎች 41.9 በመቶ የሚሆኑ ሰዎችን ከድህነት ወለል በታች ከሆነ ኑሮ እንዳላቀቁ ጠቅሰዋል።

በፈረንጆቹ 2022 ላይ ግን በመሰል ፖሊሲዎች ከድህነት ኑሮ የተላቀቁ ሰዎች ድርሻ 39.3 በመቶ እንደሆነ በጥናት መረጋገጡን ሞላ(ዶ/ር) ነግረውናል።
ጥናቱ ሰዎች እየከፋ በመጣ ድህነት ምክንያት ለምርቶች ያላቸውን ፍላጎት እንዲቀንሱ እያደረገ ስለመምጣቱ ማሳየቱንም ነግረውናል።
በጣም መሰረታዊ የሚሏቸውን የፍጆታ ምርቶች ብቻ በመጠቀም ሌሎቹን እየተዉ ነው ብለዋል።
በኢትዮጵያ እስከ ፈረንጆቹ 2019 ድረስ አጠቃላይ ምርት ከህዝቡ አጠቃላይ ፍላጎት የተሻለ እንደነበር የጥናቱን ውጤት መሰረት አድርገው ዶክተር ሞላ ነግረውናል።
ከ2019 በኋላ ግን አጠቃላይ ፍላጎትም እየቀነሰ መጥቷል ብለዋል። ሰዎች ፍላጎት ቢኖራቸውም የመግዛት አቅማቸው በመዳከሙ ምክንያት የታየ ለውጥ እንደሆነ ነው ያስረዱን።
ሰዎች ለምርቶች ያላቸው ፍላጎት ሲቀነስ አጠቃላይ የሀገር ኢኮኖሚ እንደሚጎዳ እና ስራ አጥነትም እንደሚባባስ ዶክተር ሞላ ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ እየከፋ ነው ለሚባለው ድህነት በቀዳሚ ምክንያትነት የሚጠቀሰው የዋጋ ግሽበት ነው።
የዋጋ ግሽበት በቶሎ ካልተገታ ድህነትን ከማክፋት አልፎ በህዝቡ አካላዊ እና ስነ ልቦናዊ ጤና ላይም ችግር እንደሚፈጠር ሞላ(ዶ/ር)አሳስበዋል።
በየአካባቢው የሚታዩ የፀጥታ ችግሮችም በኢትዮጵያ ድህነትን ማባባስ ላይ አስተዋጽኦቸው ከፍ ያለ እንደሆነ ተጠቅሷል።
ተመራማሪው ዶክተር ሞላ አለማየሁ እንደሚሉት የፀጥታ ችግሮቹ ብዙ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎችን እያስተጓጎሉ ነው።
በመንግስት ስራ ላይ የሚውሉ ፖሊሲዎች በርግጥም ደሃ ተኮር ናቸው ወይ? የሚለውን ማረጋገጥ የችግሩ አንዱ መፍትሄ ነው ተብሏል።
በተለይም በከተሞች የሚሰሩ የልማት ፕሮጀክቶች የአብዛኛውን ህዝብ ኑሮ የሚደግፉ ናቸው ወይ? የሚለውን ማረጋገጥ ይገባል ሲሉ ዶክተር ሞላ ተናግረዋል።
ንጋቱ ረጋሣ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s
📌 Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
📌 Linkedin : https://shorturl.at/21bFN












Comments