''ያለአግባብ ክፍያ መፈፀሙ የተረጋገጠ15 ቢሊዮን ብር አሁንም ተመላሽ አልሆነም’’
- 7 days ago
- 1 min read
ሰኔ 11/2018
በተለያዩ መስሪያ ቤቶች ያለአግባብ የተፈፀመ ክፍያ መሆኑ ተረጋግጦ ለመንግስት ተመላሽ እንዲደረግ ከታዘዘው ገንዘብ ወደ 15 ቢሊዮን ብር አሁንም ተመላሽ አልሆነም ተባለ፡፡
ተጨማሪ ከ23 ሺህ ዶላር በላይም ወደ መንግስት ካዝና መመለስ ሲኖርበት መ/ቤቶቹ ተመላሽ እንዳላደረጉ የተናገረው የፌዴራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ነው፡፡
የመንግስትና የህዝብ ሀብት ባክኖ እንዳይቀር በቢሊዮን የሚቆጠረው ብር ተመላሽ እንዲሆን በድጋሚ ለመስሪያ ቤቶቹ ማሳሰቢያ ሰጥቻለሁ ብሏል፡፡
በ2016 በጀት ዓመትና ከዚያ በፊት ከህግ ውጪ የተፈፀሙ ክፍያዎች መሆናቸው በሒሳብ ምርመራ ተረጋግጦ 21 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር እና ከ23 ሺህ ዶላር በላይ ወይምበአሁኑ ምንዛሪ ከ3 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ለመንግስት ተመላሽ እንዲሆን ጥፋቱን የፈፀሙ ተቋማት በደብዳቤ ተጠይቀው ነበር ተብሏል፡፡
ከመካከሉ ለመንግስት ተመላሽ የተደረገው 31 በመቶው ወይም 6 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብሩ ብቻ መሆኑን የፌዴራል ዋና ኦዲተር የ2017 በጀት ዓመት የኦዲት ሪፖርት ያሳያል፡፡
ያላግባብ ወጭ ተደርጓል፤ ለመንግስት ይመለስ የተባለው እና በውጭ ምንዛሬ 23,200 ዶላር ግን መቶ በመቶ ለመንግስት ሳይመለስ ቀርቷል ይላል ሪፖርቱ፡፡

የዋና ኦዲተር የኦዲት ግኝት ሪፖርት ዛሬ ለህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ቀርቧል፡፡
ከህግ ውጭ የተከፈሉ እና ለመንግስት መመለስ አለባቸው የተባሉት በአብዛኛው በጉምሩክና ፣ የገቢዎች ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች እንዲሁም በዩኒቨርስቲዎች የተፈፀሙ መሆናቸውን ሪፖርቱ ያሳያል፡፡
ከመካከላቸው ግን ከ32 እስከ 99 በመቶ ያላግባብ ያወጡትን ገንዘብ የመለሱ ተቋማትም አሉ፡፡
እንደማሳያ የኮምቦልቻ ጉምሩክ ቅርንጫፍ ከ800 ሚሊዮን ብር በላይ ፣ የኤርፖርት ጉምሩክ 621 ሚሊዮን ፣ አርባ ምንጭ ዩኒቨርስቲ 120.7 ሚሊዮን የቃሊቲ ጉምሩክ 3 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ያላግባብ አውጥተውት ከነበረው ገንዘብ ለመንግስት ተመላሽ አድርገዋል ተብሏል፡፡
የተጠቀሱት እና ሌሎችም ተቋማት ህግ ጥሰው ያላግባብ ወጭ ያደረጉትንና እስካሁን ለመንግስት ያልመለሱትን ወደ 15 ቢሊዮን ብር የተጠጋ ገንዘብ ተመላሽ እንዲያደርጉም ተጠይቀዋል፡፡
እንዲህ ያለው የሒሳብ አያያዝ መዝረክረክም ለመንግስት ገንዘብ መባከን ምክንያት እንዳይሆን አስፈላጊ እርምጃ ይወስድ ሲል የፌዴራል ዋና ኦዲተር አሳስቧል፡፡
ትዕግስት ዘሪሁን





Comments