የክብር ዘበኛ ወታደሮች፣ መንግስት ለመገልበጥ በተደረገው ሙከራ 15 ሚኒስትሮችና ከፍተኛ ሹማምንት የተገደሉት በ1953 ዓ.ም በዛሬው ቀን ነበር፡፡
- sheger1021fm
- 10 hours ago
- 2 min read
ታህሳስ 7/2018
የክብር ዘበኛ ወታደሮች፣ መንግስት ለመገልበጥ በተደረገው ሙከራ 15 ሚኒስትሮችና ከፍተኛ ሹማምንት የተገደሉት በ1953 ዓ.ም በዛሬው ቀን ነበር፡፡
ከከፍተኛ ሹማምንቱ በተጨማሪ፣ ከመፈንቅለ መንግስቱ ወገን የሆኑት የፖሊስ ጠቅላይ አዛዡና የፀጥታ ዳይሬክተሩ የሞቱት በዚያው እለት ነበር፡፡
ብርጋዲየር ጄኔራል መንግስቱ ነዋይ ፣ በመሩት መፈንቅለ መንግስት፣ ታህሳስ 4 ምሽት በቁጥጥር ስር የዋሉት፣ የአፄ ኃይላስላሴ መንግስት ሚኒስትሮችና ሌሎች ባለስልጣናት የተገደሉት ከሶስት ቀናት መታገት በኋላ ነው፡፡
መፈንቅለ መንግስቱ እንዳልተሳካላቸው ሲረዱና ተቃዋሚያቸው የምድር ሀይል ወደ ቤተ መንግስቱ ሲቃረብ ፣ በቁጥጥራቸው ስር የነበሩትን ሹማምንት በታሰሩበት የገነተ ልዑል ቤተ መንግስት ሳሎን ረሸኗቸው፡፡
ከተገደሉትም ውስጥ፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሰብሳቢና የመከላከያ ሚኒስትሩ ራስ አበባ አረጋይ ፣ የትግራይ ጠቅላይ ገዥ ራስ ስዩም መንገሻ ፣ የንግድ ሚኒስትሩ አቶ መኮንን ሀብተወልድ ፣ የውጭ ጉዳይ ምክትል ሚኒስትሩ አቶ ዳዊት እቁብ እግዚእ የማስታወቂያ ምክትል ሚኒስትሩ አቶ አምደሚካኤል ደሳለኝ፣ የሃገር ግዛት የፀጥታ ምክትል ሚኒስትሩ አፈንጉስ እሸቴ ገዳ ፣ አርበኛውና የህግ መወሰኛ ምክር ቤት አባል ደጃዝማች ለጥይበሉ በጠቅላላው 15 ሹማምንት ናቸው፡፡
ቤተ መንግስቱን ለመቆጣጠር በተደረገው የተኩስ ልውውጥም የመፈንቅለ መንግስቱ ደጋፊዎች የነበሩት የፖሊስ አዛዡ ብርጋዲየር ጀኔራል ፅጌ ይቡ ፣ የደህንነት ሹሙ ኮሎኔል ወርቅነህ ገበየሁ ከክቡር ዘበኛ መኮንኖች ጋር ተገደሉ፡፡
መፈንቅለ መንግስቱን የጠነሰሱት እነ ብርጋዲየር ጄኔራል መንግስቱ ነዋይ የኢትዮጵያ ሕዝብ በአፄው ስርዓተ ተብድሏል፡፡ ተረግጧል፡፡ ተጨቁኗል፡፡ ስለዚህ የመንግስት ለውጥ ያስፈልጋል አሉ፡፡
ንጉስ ነገስቱ አፄ ኃይለሥላሴ፣ ለጉብኝት ወደ ብራዚል ማምራታቸውን ፣ የግልበጣ ውጥናቸውን ስራ ላይ ለማዋል ፣እንደ መልካም አጋጣሚ ቆጠሩት፡፡
ታህሣስ 4/1953 ምሽት ላይ አልጋ ወራሹንና ቁልፍ ቁልፍ የንጉሱን ሹሞችና ባለሟሎችን እቴጌ ታመዋል እያሉ ወደ ክብርዘበኛ ጽ/ቤት ጠርተው ሰበሰቧቸው፡፡
የግልበጣው ጠንሳሾች ፣አብዛኛውን የአዲስ አበባ ክፍል በእጃቸው ካስገቡ በኋላ ባገቷቸው በንጉሱ ልጅ አልጋወራሽ አስፋው ወሰን ድምፅ ፣ የአፄ ኃይለ ስላሴ መንግስት መወገዱን አወጁ፡፡
የንጉሱ ታማኞች ፣ መፈንቅለ መንግስቱን ለማክሸፍ በፍጥነት ተንቀሳቀሱ፡፡ የጦር ኃይሎች ኢታማዥር ሹም ሜጄር ጄኔራል መርዕድ መንገሻ የሚመሩት የምድር ጦር ሃይል፣ የአየር ሀይልን ከጎኑ አሰለፈ፡፡
የክብር ዘበኞችን እንቅስቃሴ ለማኮላሸት ተንቀሳቀሰ፡፡
መፈንቅለ መንግስቱን የሚያወግዙ በራሪ ወረቀቶችም ተበተኑ፡፡
የፓትርያርኩ የአቡነ ባስልዩስ የውግዘት ቃልም ስለተበተነ የክብር ዘበኛ ሰራዊት ልቡ ተከፈለ፡፡
በሶስተኛው ቀንም የክብር ዘበኛ ጦር ተበትኖ እጁን ሰጠ፡፡
መሪዎቹም ያገኟቸውን ሹማምንት ገድለው ሸሹ፡፡
በመጨረሻ የሞቱት ሞተው ቀሪዎቹ ተይዘው ሙከራው ተጠናቀቀ፡፡
የከሸፈው መፈንቅለ መንግስት ጠንሳሽ ከነበሩት መካከል ጄኔራል መንግስቱ ተይዘው ፍርድ ቤት ቀርበው በስቅላት እንዲቀጡ ተፈረደባቸው፡፡ ፍርዱም በአዲስ አበባ ተክለሃይማኖት አደባባይ ተፈፀመባቸው፡፡
አብዛኞቹ ሲቪሎች የሆኑ ቢያንስ 300 ሰዎች ያለቁበትና ለአራት ቀናት የቆየው በታሪክም የታህሳሱ ግርግር በሚል ቅፅል በሚታወቀው የከሸፈው የመፈንቅለ መንግስት፣ 15 ሹማምንት ከተገደሉ ዛሬ 65 ዓመት ሆነ፡፡
እሸቴ አሰፋ












Comments