የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን ጉዳይ የሚከታተል በህግ ስልጣንና ሀላፊነት የተሰጠው አካል እንዲኖር የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ጠየቀ፡፡
- 2 hours ago
- 2 min read
ሰኔ 18/2018
የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን ጉዳይ የሚከታተል በህግ ስልጣንና ሀላፊነት የተሰጠው አካል እንዲኖር የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ጠየቀ፡፡
ኮሚሽኑ ኢትዮጵያ ተቀብላ የፈረመችውንና ለሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ጥበቃ የሚያደርገውን የካምፓላ ስምምነትን የሚያስፈፅመው ረቂቅ ህግ ይፀድቅ ዘንድም ምክረ ሀሳብ ሰጥቷል፡፡
የተፈናቃዮችን ጉዳይ የሚያስተባብርና የሚከታተል በህግ ግልፅ ስልጣንና ሀላፊነት የተሰጠው አካል እንዲኖርም ኮሚሽኑ ለፓርላማ ባቀረበው የ11 ወራት ሪፖርቱ አሳስቧል፡፡

ተፈናቃዮች የተፈናቀሉበት አካባቢ ሰላምና ፀጥታ እንዲሰፍን ፣ የተወሰደባቸው ሀብትና ንብረት መመለስ የሚችልበት የፍትህ ሂደት እና ተጎጂዎች ተገቢውን ካሳ የሚያገኙበት ስርዓትን ጨምሮ የህግ ተጠያቂነት እንዲረጋገጥም ጠይቋል፡፡
እንዲሁም ለተፈናቃዮች ዘላቂ መፍትሄ የሚሉትን የመምረጥና በአማራጮች ዙሪያም በሚደረጉ ውይይቶች ላይ ትርጉም ያለው ተሳትፎ ሊያደርጉም ይገባል ተብሏል፡፡
በሌላ በኩል የተፈናቃዮች ሰብአዊ መብት አያያዝን በተመለከተ የተወሰዱ መልካም እርምጃዎች ያላቸውንም ኮሚሽኑ በሪፖርቱ ጠቅሷል፡፡
ከመካከላቸው ለአገር ውስጥ መፈናቀል ዘላቂ መፍትሄ ለማፈላለግ ብሔራዊ ስትራቴጂ ተዘጋጅቶ ወደ ስራ መገባቱ አንዱ ነው ብሏል፡፡
በተጨማሪም ከኦሮሚያ ክልል ተፈናቅለው በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሚገኙ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ መደረጋቸው ፣ የዲጂታል መታወቂያ ማግኘት እንዲችሉ ጥረት እየተደረገ መሆኑም አበረታች ጅምር ስራዎች ናቸው ይላል የኢሰመኮ ሪፖርት፡፡
በተያያዘ ጥገኝነት ፈልገው እና ጥገኝነትም ተሰጥቷቸው በኢትዮጵያ የተጠለሉ ስደተኞችን የሰብአዊ መብት አያያዝ በተመለከተም ኮሚሽኑ በሪፖርቱ አካቷል፡፡
በዚህም ከስደተኞች ጋር ተያይዞ አሳሳቢና መፍትሄ ያሻቸዋል ብሎ ከጠቀሳቸው መካከል ለአመታት በቋሚነት ጥገኝነት ጠያቂዎችን ይመዘግቡ የነበሩ መቀበያ ጣቢያዎች መዘጋታቸው፣ በአዲስ አበባ ከተማ እና በሌሎችም አካባቢዎች ቀጣይነት ባለው መንገድ ጥገኝነት ጠያቂዎች ምዝገባ እየተካሄደ አለመሆኑ ይገኙበታል ብሏል፡፡
በተጠቀሱት ምክንያቶችም ጥገኝነት ጠያቂዎች ሰነድ የላችሁም ተብለው የመንቀሳቀስ መብት ገደብ ያጋጥማቸዋል ፣ የሰብአዊ ድጋፍ አያገኙም እንዲሁም ሌሎችንም የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እንዲጋለጡ አድርጓቸዋል ተብሏል፡፡
በተጨማሪም የስደተኝት ሁኔታ አወሳሰን ሳይፈፀምላቸው ያለበቂ መሰረታዊ አገልግሎት በመጠለያ ጣቢያዎች ለረዥም አመታት የሚቆዩ መሆናቸውም አሳሳቢ ነው ብሏል፡፡
በሌላ በኩል ስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎች በኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ አገልግሎቶች እንዲካተቱ ታስቦ ስደተኞች በተለያዩ ስራዎች በመሰማራት ራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን እንዲደግፉ በህግ መፈቀዱን በበጎ አንስቷል፡፡
በአዲስ አበባም የተወሰኑ የስደተኛ መር እና የተመላሾች መር ማህበራት ተቋቁመው ውጤታማ ስራ እየሰሩ መሆናቸውን አበረታች ነው ብሎታል የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በ11 ወራት ሪፖርቱ፡፡
ትዕግስት ዘሪሁን





Comments