ኢትዮጵያ ባለፉት 5 ዓመት ውስጥ ለባህሉ ዘርፍ ከአጠቃላይ በጀቷ 0.11 በመቶ ብቻ መሆኑን ጥናት አሳየ።
- 1 hour ago
- 2 min read
ሰኔ 11/2018
ኢትዮጵያ ባለፉት 5 ዓመት ውስጥ ለባህሉ ዘርፍ ከአጠቃላይ በጀቷ 0.11 በመቶ ብቻ መሆኑን ጥናት አሳየ።
ይሁን እንጂ የባህል ዘርፍ ከግብርና ቀጥሎ በሀገሪቱ ሁለተኛው የሥራ ዕድል ፈጣሪ ዘርፍ ስለመሆኑም ተነግሯል።
ይህ ጥናት የቀረበው ሠላም ኢትዮጵያ የተሰኘ መንግስታዊ ያልሆነ ተቋም የባህልና ፈጠራ ኢንዱስትሪ በኢኮኖሚው ላይ ያለውን አስተዎፅኦ በተመለከተ ከዘርፉ ባለሙያዎችና ከመንግስት ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ለማድረግ ባሰናዳው መድረክ ላይ ነው።

በመድረኩ ላይ ጥናታዊ ፅሁፍ ያቀረቡት ይስማ ፅጌ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ ባለፉት 5 ዓመታት ለባህሉ ዘርፍ የመደበችው ከአጠቃላይ በጀቷ 600 ሚሊየን ብቻ ነው ብለዋል።
ይህም የ 0.11 በመቶ ድርሻ እንደሚይዝ ይስማ (ዶ/ር)አንስተዋል።
የአፍሪካ ህብረት በ2030 ከአጠቃላይ በጀት 1 በመቶውን ለባህሉ ዘርፍ እመድባለሁ ባለው ዕቅድ ውስጥ ኢትዮጵያ በዕቅዱ ውስጥ ያለችበት ቢሆንም ዕቅዱን ለማሳካት ግን ቁጥሩ ሩቅ መሆኑን አጥኚው አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ ለባህሉ ዘርፍ የምትመድበው በጀት 1 በመቶ እንዲሆን አሁን ያለው የኢትዮጵያ በጀት በ9 ዕጥፍ ማደግ አለበት ብለዋል።

በክልሎች ያለው በጀት እና የባህል ትኩረት ደግሞ ከዚህም ያነሰ መሆኑን አንስተዋል።
ይስማ (ዶ/ር) 1 በመቶ የሚለው ዕቅድ ለማሳካት እና መንግስት ላይ ግፊት ለማድረግ ባህል ችግር ይፈታል የምንል ከሆነ አሁን ያሉ ችግሮችን በመፍታት የባህልን ጠቃሚነት ማሳየት አለብን ብለዋል።
ሀገር ባህሏን ችላ የምትል ከሆነ መሰረቷን እንዲናጋ የፈቀደች ናት እንደማለት ይቆጠራል ሲሉም አስረድተዋል።
አብርሆት ቤተ-መፅሐፍት፣ አድዋ ሙዝየም እና ሳይንስ ሙዝየም ለባህል ዕድገት ያላቸው አስተዋፅኦ የጎላ ቢሆንም የተሰሩበት የበጀት ምንጭ ማወቅ አልቻልንም ብለዋል ይስማ (ዶ/ር)።
የአዲስ አበባ ባህልና ኪነ ጥበብ ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ሂሩት ካሳው በበኩላቸው ጥናቱ የመረጃ ክፍተት አለበት አብርሆት፣ አድዋ እና ሌሎቹም የኪነ ጥበብ እና ባህል ዕድገት ላይ ትኩረት ተደርገው የተሰሩ ፕሮጀክቶች ከህዝብ ግብር በተሰበሰበ የከተማ አስተዳደር የተሰራ ፕሮጀክት ነው ብለዋል።

ዶ/ር ሂሩት ጥናቱ 1 በመቶ በጀት ይመደብልን የሚል ሃሳብን የያዘ ነው፣ 1 በመቶ ቢበጀት ምን ይሰራበታል የሚለውን አላካተተም ሲሉም ተችተዋል።
በመሰረቱ እኔ ባለሁበት ዘርፍ በበጀት ችግር መስራት አልቻልንም የሚል አካል የለም፣ ካለም ይምጣ፣ የሚሰራ ነገር ኖሮ በጀት የተከለከለበት ጊዜ የለም ብለዋል።
በውይይቱ ላይ የተሳተፉ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች በበኩላቸው የበጀት ዕጥረት አንዱ ችግር ነው፣ አሁን ስቱዲዮ እንግባ ብንል ማን ይሰጠናል ሲሉ ጠይቀዋል።
ዶ/ር ሂሩት ሲመልሱም ጥናቱ አንድ በመቶ ይመደብ የሚለው ለመንግስት ተቋማት እንጂ ለግለሰቦች አይደለም፣ እየተነጋገርን ያለነው በባህል ዘርፍ ላይ ስለሚሰሩ የመንግስት ተቋማት እንጂ ስለ ግለሰቦች አይደለም ብለዋል።
ስለዚህ እናንተ በግል ብትጠይቁ በጀት ላይፈቀድ ይችላል፣ በመንግስት ተቋም ደረጃ ግን የሚሰራ ነገር ኖሮ እኔ ብጠይቅ የሚከለክል የለም ሲሉ መልሰዋል።
ትልቁ ችግር በጀት ሳይሆን ምን እንስራ የሚለው ጉዳይ ነው ያሉት ሂሩት (ዶ/ር) ጥናቶቻችንም እዚያ ላይ ቢያተኩሩ ሲሉ መክረዋል።
ንጋት መኮንን




Comments