top of page

አነስተኛ ይዞታ ያላቸውን አርሶ አደሮች፣ አርብቶ አደሮችና ከፊል አርብቶ አደሮችን በተናጠል ከመስራት ተላቅቀው በንግድ መርህ የአግሪ-ቢዝነስ ኩባንያ እንዲያደራጁ የሚፈቅድ ረቂቅ አዋጅ ተሰናደ፡፡

  • Jun 8
  • 2 min read

ሰኔ 1/2018


አነስተኛ ይዞታ ያላቸውን አርሶ አደሮች፣ አርብቶ አደሮችና ከፊል አርብቶ አደሮችን በተናጠል ከመስራት ተላቅቀው በንግድ መርህ የአግሪ-ቢዝነስ ኩባንያ እንዲያደራጁ የሚፈቅድ ረቂቅ አዋጅ ተሰናደ፡፡


በአዋጁ መሰረት የሚቋቋመው ኩባንያ ከውጪ የሚያመጣቸውን ማንኛውም ማሽነሪዎች ግብዓቶች እና መለዋወጫዎች ከግብር ነጻ ይደረጋሉ ፤ አባላት በሚያገኙት የትርፍ ክፍፍል ላይ የገቢ ግብር አይከፍሉም፡፡


ረቂቁ አነስተኛ አምራቾች እንደ ህጋዊ የንግድ ተቋም ተቆጥረው ከባንክ ብድርና ፋይናንስ እንዲገኙ እና በከፍተኛ የንግድ ውሎች ውስጥ እንዲሳተፉ ያደርጋል ተብሏል፡፡



ባለፈው ግንቦት 27 ቀን 2018 ዓ.ም ፓርላማው ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ ለግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የመራው የግብርና ቢዝነስ ኩባንያ አዋጅ አነስተኛ አርሶ አደሮች ቀድሚያ የውጭ ምንዛሬ እንዲገኙ ፣ በምርታቸው ላይ ዋጋ እንዲወስኑ፣ የፋይናስ እና ኢንሹራንስ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እንዲሁም ምርቶቻቸውን በቀጥታ ወደ ውጭ እሴት ጨምረው እንዲልኩ የሚያስችል እንደሆነ በረቂቅ አዋጁ ማብራሪያ ላይ ተዘርዝሯል፡፡


ነባር አሰራሮች አርሶ አደሩ ምርቱን በጥሬው እንዲያቀርብ እንጂ እሴት ጨምሮ እንዲሸጥ የሚያስችል፣ የተሟላ የባለቤትነትና የትርፍ ክፍፍል መዋቅር የማይሰጡ ፣ አምራቹ ከድካሙ ጋር የሚመጣጠን ትርፍ ከማግኘት ይልቅ በደላሎችና ባልተቀናጀ የግብይት ሰንሰለት ውስጥ እንዲወሰን የሚደርጉ መሆናቸው የግብርና ቢዝነስ ኩባንያ አዋጅ እንዲዘጋጅ ምክንያት መሆናቸው ተጠቅሷል፡፡


አነስተኛ አርሶና አርብቶ አደሮች በተናጠል ምርት የሚያቀርቡ በመሆናቸው በገበያ ላይ የመደራደር አቅማቸው ዝቅተኛ ነው ያለው ረቂቅ አዋጁ እነዚህን አምራቾች በኩባኒያ ደረጃ በማደራጀት ምርታቸውን በጋራ እንዲያቀርቡ፣ የተሻለ ዋጋ እንዲያገኙና ደላሎች በመሃል የሚፈጥሩትን ተጽዕኖ መቀነስ ዓላማው እንደሆነ አስረድቷል፡፡



የግብርና ቢዝነስ ኩባንያ አዋጅ የኩባኒያ አመሰራረትን በተመለከተ በክፍል ሁለት ሲያስረዳ በግብርና የስራ መስክ የተሰማሩ የአነስተኛ ይዞታ አምራች ግለሰቦች ወይም ድርጅቶች ጥምረት ነው፡፡


እንዲሁም በክላስተር በግብርና የስራ መስክ የተሰማራ ድርጅት ራሱን ወደ ግብርና ቢዝነስ ኩባኒያ ሲለውጥ ነው ይላል፡፡

የመስራች አባላትን ብዛት ሲዘረዝር ደግሞ በአዝርዕት ሰብሎች ከሆነ ቢያንስ 300፣ በአትክልትና ፍራፍሬ ሰብሎች ወይም በእንሰሳት እርባታ ከሆነ ቢያንስ 150 መሆን እንዳለባቸው ደንግጓል፡፡


ከላይ ከተጠቀሰው ቁጠር ያለነሰ ያለው የግብርና ቢዝነስ ኩባኒያ መስራቾች የአካባቢ ነባራዊ ሁኔታዎችና የኢኮኖሚ አዋጭነትን መሠረት በማድረግ በሚወጣ መመሪያ እንደሚወሰንም ተጠቅሷል፡፡


ማንኛውም የግብርና ቢዝነስ ኩባንያ የሚመሰረተው ደግሞ ከታወጀው የድርሻ መጠን ሃያ አምስት ከመቶ ሲከፈል እንደሆነ ተመላክቷል፡፡


የድርሻ ዋጋ እና የካፒታል መጠን በተመለከተ ደግሞ በግብርና ቢዝነስ ኩባንያ ውስጥ የሁሉም ድርሻ ዋጋ እኩል መሆን እንዳለበት፤ የኩባንያው የአንድ ድርሻ ዋጋ ከአንድ ሺህ ብር በታች መሆን እንደማይችል፣ የኩባንያው ዝቅተኛው የተከፈለ ዋና ካፒታል ከአንድ ሚሊዮን 500 መቶ ሺህ ብር ያነሰ ሊሆን እንደማይገባ ዘርዝሯል፡፡


በረቂቁ መሰረት ኩባኒያው የሚደራጅበት የግብርና ስራ ዘርፍ በዋናነት የአዝርዕት ሰብሎች ከሆነ አንድ አባል ሊገዛ የሚችለው ዝቅተኛው ድርሻ አምስት ሲሆን በአትክልትና ፍራፍሬ ሰብሎች ወይም በእንስሳት እርባታ ከሆነ ዝቅተኛው ድርሻ አስር መሆን አለበት፡፡



ማንኛውም የኩባንያው አባል በጠቅላላ ጉባኤ እንዲሸጥ ከተወሰነው የድርሻ መጠን ከ15 በመቶ በላይ ድርሻ መግዛት አይችልም፡፡


የግብርና ቢዝነስ ኩባኒያ የስራ መስኮች ደግሞ ምርጥ ዘር፣ ማዳበሪያ፣ የእርሻ መሳሪያዎች፣ አግሮ ኬሚካል፣ የእንስሳት እና ሌሎች የግብርና ግብዓቶችን እና መገልገለያ መሳሪዎችን ማቅረብ፣ ግብርና ምርት ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎችን ማቋቋም ይሆናል በአዋጁ መሰረት፡፡


ግብርና ቢዝነስ ኩባንያ በማንኛውም ጊዜ ከስራው ጋር በተያያዘ የሚያስፈልጉትን ከውጪ የሚገቡ የግብርና ግብዓቶችና ቴክኖሎጂዎች፣ ተሽከርካሪዎች እና ለእነዚሁ መሳሪያዎች እና ተሽከርካሪዎች የሚውሉ የመለዋወጫ እቃዎች፣ የግንባታ ዕቃዎች ከታክስ ነፃ እንደሚደረጉለት ረቂቁ አስረድቷል፡፡


እነዚህን ግብዓቶች ለማምጣትም ቅድሚያ የውጪ ምንዛሪ ያገኛሉ፡፡


የግብርና ቢዝነስ ኩባንያ አባላት ያመረቱትን የግብርና ምርት ሲሸጡ ወይም ከኩባኒያው በሚያገኙት የትርፍ ክፍፍል ላይ የገቢ ግብር አይከፍሉም፡፡


ኩባንያው ከሚያገኘው ገቢ ላይ ግን በገቢ ግብር አዋጁ መሰረት ግብር ይከፍላል፡፡


ያሬድ እንዳሻው

Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2026 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page