top of page

ነሀሴ 9 2017 - የወንጀል ምጣኔ በ43 በመቶ ቀንሻለሁ ሲል የአዲስ አበባ ፖሊስ ተናገረ

  • sheger1021fm
  • Aug 15
  • 2 min read

በአዲስ አበባ በወንጀል መከላከል በሠራኋቸው ስራዎች የወንጀል ምጣኔውን በአርባ ሶስት በመቶ ቀንሻለሁ ሲል የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ተናገረ፡፡


በሌላ በኩል የሚፈጸሙ ወንጀሎችን ጥቆማ ለመስጠት ተቋሙ ከዚህ ቀደም ሲጠቀምበት ከነበረው የስልክ መስመር በተጨማሪ ዘመናዊ መተግበሪያን በመጠቀም ከነማስረጃዎች ጭምር ጥቆማ መስጫ ቴክኖሎጂን በስራ ላይ ማዋሉን ተናግሯል፡፡


የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት የሚዲያ ማስተባበሪያ ኃላፊው ረዳት ኢንስፔክተር ዳዊት እርገጤ እንደነገሩን በከተማዋ ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን ለመከላከል በ2017 የተከወኑ ስራዎች የወንጀል ምጣኔ እንዲቀንስ አድርገዋል ብለዋል፡፡


የከተማው ነዋሪ ከፖሊስ ጎን ሆኖ በመስራቱም ነው እነዚህ ውጤቶች የመጡት ለፖሊስ መረጃ ከመስጠት ጀምሮ ሁሉም ሰው አካባቢውን ወጥቶ መጠበቁ አስተዋጽኦ ማድረጉን ጠቅሰዋል፡፡


በተጨማሪም የወንጀል መከላከል ስራን ለማገዝ ተቋሙ ዘመናዊ አሰራሮችን እየተከተለ ነው ለወንጀል ጥቆማ የሚሰጡ ሰዎች ያሉበትን አድራሻ በቀጥታ መለየትና በአካባቢው ባሉ የፖሊስ አባላት ፈጣን ምላሽ እንዲያገኙ ማድረግ ላይ የተጀመሩ ስራዎች መኖራቸውን ረዳት ኢንስፔክተር ዳዊት ተናግረዋል፡፡


ዋናው ትልቁ ነገር ለወንጀል መቀነሱም ለከተማዋ ሰላምና መረጋጋትም ፖሊስ ብቻውን ሰርቶ ያመጣው ነገር ይኖራል የሚል እምነት የለንም ያሉት ኃላፊው ነዋሪዎች መረጃ ከመስጠት ጀምሮ አካባቢያቸውን እስከመጠበቅ ድረስ ከኛ ጋር አብረው እየሰሩ በመሆኑ ምስጋና እናቀርባለን ብለዋል፡፡


ለፖሊስ የጥቆማ መስጫ መንገዱንም ከስልክ በተጨማሪ ከፌዴራል ፖሊስ ጋር በመሆን የዜጎች ተሳትፎ መተግበሪያ በማበልፀግ ወደ ስራ መግባቱንና ጥቆማዎች ሲሰጡ ማስረጃ ማቅረብ የሚያስችል በመሆኑ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን በዝርዝር ለማወቅና እርምጃ ለመውሰድም የሚያግዝ ሆኗል በዚህም የወንጀል ምጣኔ እንዲቀንስ አድርጓል ተብሏል፡፡


ለፖሊስ መረጃ መስጠት የሚፈልግ ማንኛውም ዜጋ ከ991 የፖሊስ የመረጃ ስልክ በተጨማሪ መተግበሪያውን በማውረድ በቀላሉ ለፖሊስ አለኝ የሚለውን ማስረጃ በፎቶ በቪዲዮ በድምጽ እንዲሁም ሊንክ በመላክ ጥቆማ መስጠት ይቻላል ተብሏል፡፡


በአዲስ አበባ በፀጥታ ጥበቃና የወንጀል ስጋቶችን ከዚህ በላይ ለመቀነስ የሚሰሩት ስራዎች በ 2018 በጀት አመትም እንደሚቀጥሉ የተናገረው የአዲስ አበባ ፖሊስ ከተለያዩ ክፍለ ከተሞች የሚሰጡ መረጃዎችን በመከታተል የፀጥታ ስጋት ባሉባቸው አካባቢዎች ላይ አሰሳና ፍተሻ እንደሚደረግ ተናግሯል፡፡


ምህረት ስዩም


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…




Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page