ነሀሴ 9 2017 - ሀሰተኛ የግዢ ደረሰኝ በማዘጋጀትና በማሰራጨት የተጠረጠሩ አስራ ሁለት ሰዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ።
- sheger1021fm
- Aug 15
- 1 min read
በዚህም መንግስት ሊያጣ የነበረውን ከ480,000,ዐዐዐ ብር በላይ ማዳን መቻሉንም የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ በላከልን መግለጫ ተናግሯል።
ወንጀሉ የተፈፀመው በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ አራት ልዩ ቦታው ፊስቲቫል ህንፃ ሀያ ሁለት ማዞሪያ አካባቢ እና በልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 ክልል ልዩ ቦታው አብደላ ህንፃ ልህቀት ህንፃ እንዲሁም ጌጃ ሰፈር በሚገኘው ብሌን ፕላዛ ህንፃ ውስጥ ለንግድ ስራ በሚል ቢሮ ተከራይተው ከ2015 ዓ/ም እስከ 2017 ዓ/ም ባለው ጊዜ ውስጥ ነው ተብሏል።

ተጠርጣሪዎቹ የተለያዩ የጎዳና ተዳዳሪዎችን እና በዝቅተኛ ገቢ የሚተዳደሩ ሰዎችን በመመልመልና በገንዘብ በመደለል ግለሰቦቹ ሀሰተኛ ስም ተጠቅመው የቀበሌ መታወቂያ፣ ዲጂታል ፋይዳ መታወቂያ፣ መንጃ ፈቃድ እና የቁጠባ ሂሳብና የባንክ ደብተር እንዲሁም የውክልና ሰነዶችን አዘጋጅቶ የንግድ ፈቃድ ማወጣታውን ፖሊስ ጠቅሷል።
ከተለያዩ የሽያጭ መመዝገቢያ መሳሪያ አቅራቢ ድርጅቶች ጋር የሽያጭ መመዝገቢያ መሳሪያ በማውጣት፣ የእጅ በእጅ የሽያጭ ደረሸኝ በማሳተም፣ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የገቢዎች ቢሮ ልደታ ክፍለ ከተማ አነስተኛ ግብር ከፋዮች ቅርንጫፍ ፅ/ቤት የሚል ሀሰተኛ ክብ ማህተም እና በዚሁ መስሪያ ቤት የሚታወቅ የመረጃ ኦፊሰር ስም የያዘ ቲተር በማዘጋጀት ሀሰተኛ ደረሰኞችን ለተለያዩ ድርጅቶችና ግለሰቦች እያዘጋጁ ሲያሰራጩ እንደነበር ፖሊስ አስረድቷል።
ፖሊስም በዚህ ተግባር የጠረጠራቸውን አስራ ሁለት ግለሰቦችን ይዞ ምርመራ እያጣራባቸው እንደሚገኝም የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ የሙስና ገቢዎችና ሸማቾች ወንጀል ምርመራ ዳይሮክቶሬት አስረድቷል።
ተጠርጣሪዎች ሲገለገሉባቸው የነበረ ኮምፕዩተር፣ ፕሪንተሮች፣ ስካነር፣ ሀርድ ዲስክ፣ የሽያጭ መመዝገቢያ ማሽን እና ህገ-ወጥ ክብ ማህተም እንዲሁም ተዘጋጅተው ለግለሰቦች ሊሰራጩ የነበረ ሀሰተኛ የግዢ ደረሰኞች መያዙን ተነግሯል።
ንጋቱ ሙሉ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s












Comments