ነሀሴ 6 2017 - አዲስ አበባ በመጪዎቹ ዓመታት ኮድ አንድ ታክሲዎችን ትታ ወደ አውቶብስ የትራንስፖርት ስርዓት ልትገባ ነው ተባለ
- sheger1021fm
- Aug 12
- 1 min read
አዲስ አበባ በመጪዎቹ ዓመታት ኮድ አንድ ታክሲዎችን ትታ ወደ አውቶብስ የትራንስፖርት ስርዓት ልትገባ ነው ተባለ።
የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ኦፕሬሽን ዘርፍ ም/ኃላፊ አቶ ዳኛቸው ሽፈራው የከተማዋ የወደፊት የትራንስፖርት ፖሊሲና ስትራቴጂ ከኮድ አንድ ታክሲዎች ይልቅ አውቶብስና ከ25 ሰው በላይ የሚጭኑ ሜትር ታክሲዎችን የሚያበረታታ ስለሆነ ከተማዋ ወደዚያው የትራንስፖርት ስርዓት ትገባለች ሲሉ ነግረውናል።
አንድ አውቶብስ የ8 ታክስዎችን ያህል ይጭናል፣ ከመንገድ መጨናነቅ፣ ከተመጣጣኝ የጉዞ ታሪፍ፣ ከነዳጅ ቁጠባና ከአየር ብክለት አንፃር አውቶብስን ጨምሮ ከ25 ሰው በላይ የሚጭኑ የብዙሃን ትራንስፖርት አገልግሎት ተጠቃሚ መሆን ለከተማዋ ተመራጭ ነው ያሉት ኃላፊው ማህበረሰቡ ብዙሃን ትራንስፖርት የመጠቀም ልምዱን እንዲያሳድግ መክረዋል።

የትራንስፖርት ቢሮ ኦፕሬሽን ዘርፍ ምክትል ኃላፊው አሁን ከተማዋ ውስጥ ያሉ #ኮድ_አንድ_ታክሲዎች አብዛኛዎቹ አሮጌና የከተማዋን የታክሲ መስፈርት ስለማያሟሉ ጭምር ከትራንስፖርት ስርዓቱ መውጣታቸው ግድ ነው ብለዋል።
ኮድ አንድ ታክሲዎች ከትራንስፖርት አገልግሎት ውጪ ሲሆኑ ሰዎችን ከስራ ገበታ አያፈናቅልም ወይ የሚል ጥያቄ ያነሳንላቸው ኃላፊው በመንግስት ድጋፍ ኮድ አንድ ታክሲዎችን ከ25 ሰው በላይ ወደ ሚጭኑ ሜትር ታክሲዎች የማሳደግ ሥራ ይሰራል ብለውናል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከአዲሱ ገብያ መገናኛና ከመገናኛ አዲሱ ገበያ፣ ከጋርመንት መገናኛና ከመገናኛ ጋርመንት እንዲሁም ከጀሞ መገናኛና ከመገናኛ ጀሞ የሚጭኑ ታክሲዎች ክልከላ የፖሊሲና ስትራቴጂው አንድ አካል ነው ያሉት ኃላፊው በዋናነት ግን እንደ ጀሞ ጋርመንትና አዲሱ ገብያ ያሉ በከተማዋ ረጃጅም ጉዞዎች ላይ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ታክሲዎች መንገድ እያቆራረጡ ከጉዞ ታሪፍ በላይ ሲያስከፍሉ ስለነበር ነው ብለዋል።
በአዲሱ የትራንስፖርት ፖሊሲና ስትራቴጂ ከ2018 ጀምሮ ከጀሞ በቄራ አድርጎ ፒያሳ የሚደርስ ፈጣን የአውቶብስ መንገድ ይጀመራል የተባለ ሲሆን ከሁለት ዓመት በኋላም አዲስ አበባ ከታክሲዎች ጋር የማይገናኝ ፈጣን የአውቶብስ ትራንስፖርት አገልግሎት እንደሚኖራት ከኃላፊው ሰምተናል።
ንጋት መኮንን
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s








