ነሀሴ 5 2017 - በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በከተማ ደረጃ ዘርዘር ያለ የአየር ትንቢያ መረጃ መሰጠት ተጀመረ፡፡
- sheger1021fm
- Aug 11
- 2 min read
በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በከተማ ደረጃ ዘርዘር ያለ የአየር ትንቢያ መረጃ መሰጠት ተጀመረ፡፡
ስራው ከአዲስ አበባ ከተማ መጀመሩንም ሰምተናል፡፡
በከተማዋ ባሉ በሁሉም ክፍለ ከተሞች የሚኖረውን እለታዊ የአየር ትንቢያ መስጠት መጀመሩን የኢትዮጵያ ሜቴዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ነግሮናል፡፡
ከዚህ በኋላ አዲስ አበባ በየሰፈሮቿ የሚኖረው የአየር ጠባይ በየቀኑ ተተንትኖ ይቀርባል ተብሏል፡፡
ከኢንስቲትዩቱ እንደሰማነው ከዚህ ቀደም ለአዲስ አበባ ከተማ ሲሰጥ የነበረው የትንቢያ መረጃ እንደማንኛውም የሃገሪቱ ከተሞች ጥቅል የሆነ መረጃ ነበር፡፡
ከከተማዋ ስፋት፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ፋይዳ አንፃር በከተማ ደረጃ ትንቢያ መስጠት በማስፈለጉ ኢንስቲትዩቱ የከተማ ትንቢያ ለመስጠት የሚያስችል ሞዴል አዘጋጅቶ ሲሰራበት እንደቆየ ጠቁሟል፡፡
አቶ ታረቀን አበራ በኢትዮጵያ ሚቴዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት የተቀናጀ ዘርፍ ተኮር የሜቴዎሮሎጂ አገልግሎት መሪ ስራ አስፈፃሚ ናቸው፡፡

እርሳቸው እንደሚሉት ሃገር አቀፍ የአየር ትንቢያ የሚሰራበትና በከተማ ደረጃ የሚሰራበት ሞዴል ይለያያል፤ትንቢያው የሚሸፍነው የቦታ መጠን ባነሰ ቁጥር ተዓማኒነቱ እየጨመረ ይመጣል፡፡
አሁን ለአዲስ አበባ የተሰራበት ሞዴል የተወሰደው የከተማ የአየር ትንቢያ በመስጠት ከሚታወቀው ዩኬሜት ከተሰኘው የእንግሊዞች ሞዴል እንደሆነ አቶ ታረቀኝ ጠቁመው የእንግሊዝ መንግስት ስራውን ለመደገፍ ፍላጎት አሳይተዋል ብለውናል፡፡
የከተማዋን ትንቢያ ለመስራት ባለሙያዎችን ከመመደብ ውጪ ተጨማሪ መሳሪያዎች አላስፈለጉም ባሉት መሳሪያዎች ነው የሚሰራው ያሉን ሃላፊው ከዚህ በኋላ መረጃዎቹን በሚቴዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ዌብሳይትና በሌሎችም አማራጮች ማግኘት ይቻላል ብለውናል፡፡
በዚህም መሰረት፤ የዛሬ ሰኞ ነሃሴ 5 ቀን 2017ዓ.ም ትንቢያ የአዲስ አበባ አካባቢዎች ከ15 እስከ 29 ሚሊ ሜትር የሚደርስ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚጠበቅ የኢንስቲትዩቱ ትንቢያ መረጃ ያሳያል፡፡
በሌላ በኩል በጥቂት የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ጫፍ አካባቢዎች ከ30 ሚሊ ሜትር በላይ ዝናብ ሊኖር እንደሚችል ተተንብዩዋል፡፡
የሚጥለው መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ የገጠ ምድር የውሃፍሰት ለመጨመር የሚረዳ ቢሆንም በተለይ የጎርፍ ተጋላጭ በሆኑ የአዲስ አበባ አካባቢዎች ተደጋጋሚነት ካለው እርጥበት ጋር ተዳምሮ መጠነኛ ጎርፍ ሊያስከትል ይችላል ሲልም ኢንስቲትዩቱ አስጠንቅቋል፡፡
በእነዚህ አካባቢዎች የጎርፍ ማፋሰሻ ቦዮችን በማጥዳት እንዲሁም የጎርፍ መቀልበሻ ቦዮችን በማዘጋጀት ጥንቃቄ ይደረግ ተብሏል፡፡
በትንቢያ መረጃዎች አሰጣጥ መሰረት ከ30 ሚሊ ሜትር በላይ የሆነ ዝናብ ከመደበኛው በላይ እንደሆነ ከኢንስቲቱዩቱ ሰምተናል፡፡
ምንታምር ፀጋው
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s








