ነሀሴ 27 2017 - ተላላፊ ያልሆኑ ህመሞችን በተመለከተ በቂ ጥናት አለመደረጉ በሽታዎቹንም ለመከላከል የባለሙያ እጥረት መኖሩ ችግሩን ተደራራቢ አድርጎታል ተባለ
- sheger1021fm
- 14 minutes ago
- 1 min read
በኢትዮጵያ ተላላፊ ያልሆኑ ህመሞችን በተመለከተ በቂ ጥናት አለመደረጉ በሽታዎቹንም ለመከላከል የባለሙያ እጥረት መኖሩ ችግሩን ተደራራቢ አድርጎታል ተባለ፡፡
በኢትዮጵያ ተላላፊ ካልሆኑ ህመሞች ውስጥ እየጨመረ የመጣው ስትሮክ ለመከላከልና ግንዛቤ መስጠት ላይ ለመስራት ያለመ የኢትዮጵያ ስትሮክ ፋውንዴሽን በባለሙያዎች ተመስርቷል፡፡
ፋውንዴሽኑ በሀገሪቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋ የመጣውን የስትሮክ ህመም ቀድሞ መከላከል፣ ህክምናና ትምህርት ላይ በስፋት ይሰራል ተብሏል፡፡
የኢትዮጵያ ስትሮክ ፋውንዴሽን መስራችና የቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር ወንድወሰን ገብረ አማኑኤል እንደሚናገሩት ተላላፊ ካልሆኑ ህመሞች ውስጥ በብዛት ከሚከሰቱና በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ታዳጊ ሀገራት ላይ ቁጥራቸው እየጨመሩ ካሉ ህመሞች አንዱ ስትሮክ ሆኗል ይላሉ፡፡

የከተማ ኑሮ፣ የአመጋገብ ሥርዓት መቀየር በተለይም የታሸጉና የተጠባበሱ ምግቦችን ማዘወተር ፣ የሰውነት እንቅስቃሴ አለማድረግ እንደ ደም ግፊት፣ ስኳር ላሉ በሽታዎች መከሰት መንስኤ ሆነዋል፤ እነዚህንም ተከትሎ ስትሮክ የመከሰት ዕድሉ ከፍተኛ መሆኑን ይናገራሉ፡፡
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህም ስትሮክ መምጣት ብቻ ሳይሆን በጣም ወጣትና አምራች የሆነውን ማህበረሰብ ማጥቃት ጀምሯል ብለዋል፡፡
ይህም ሀገሪቱ ቀድሞ ካለባት ችግር ተጨማሪ በመሆን በጤና ስርዓቱ ላይ የሚያደርሰው ተጽዕኖ መጨመሩንና ችግሩ በሀገር ምጣኔ ሃብት ላይ ጭምር የሚያርፍ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
የተለያዩ ጥናቶችን በማድረግ ባለሙያዎችን በማሰልጠንና በሌሎችም ድጋፎች በማድረግ ፋውንዴሽኑ ያግዛል የሚሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ስትሮክ ፋውንዴሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሻሎም ያዕቆብ ናቸው፡፡
በተለያየ ቋንቋ በመጠቀም በተለይ በትምህርት ቤቶች ላይ ስልጠና አንሰጣለን ይህም ህመሙ ሳይከሰት ቀድሞ መከላከል ላይ በብዙ ያግዛል ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ ተላላፊ ያልሆኑ ህመሞች ጫና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱ የተነገረ ሲሆን ህመሞቹ በስፋት ቢታዩም በቂ ባለሙያ አለመኖር፣ የህክምና ተደራሽነቱ አነስተኛ መሆንና ያለውም መረጃ ውስን መሆን ችግሩን አክብዶታል ተብሏል፡፡
ሙሉ ዘገባውን ያድምጡ….
ምህረት ስዩም
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s
Comments