ነሀሴ 22 2017 - ግብፅ ህዳሴ ግድቡን በተመለከተ እያደረገች ያለችውን ጫና ኢትዮጵያ በስጋት አንደማትመለከተው የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተናገረ።
- sheger1021fm
- 1 day ago
- 1 min read
ግብፅ ህዳሴ ግድቡን በተመለከተ እያደረገች ያለችውን ጫና ኢትዮጵያ በስጋት አንደማትመለከተው የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተናገረ።
የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጠው መግለጫ ግብፅ ህዳሴ ግድቡን በተመለከተ የዲፕሎማሲ ጫና ለመፍጠር የምታደርገው ጥረት ለኢትዮጵያ ስጋት አይሆንም ሲል ተናግሯል።
የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነቢያት ጌታቸው የግብፅ አካሄድ ስጋት የማይሆነው ከዚህ ቀድምም የነበረ ስለሆነ ነው ብለዋል።
የህዳሴ ግድቡ ምርቃት መቃረቡን ያስታወሱት አምባሳደር ነቢያት ጌታቸው የቅኝ ግዛት እሳቤዎች ተቀባይነት የላቸውም ብለዋል።
በለፉት 14 ዓመታት በመላው ኢትዮጵያዊያን ድጋፍ ከፍተኛ መሰናክሎችን አልፎ ህዳሴ ግድቡ የመመረቅያው ዋዜማ ላይ እንገኛለን ያሉት አምባሳደሩ ምርቃቱንም ኢትዮጵያዊያን እና የኢትዮጵያን በጎ የሚመኙ አብረውን የሚያከብሩት ይሆናል ሲሉ አስረድተዋል፡፡
ለምርቃቱ በስም ያልዘረዘሯቸው እንግዶች እንደተጋበዙ የተናገሩት ነብያት ጌታቸው ጊዜው ሲደርስ እነማን እንደሚገኙ የምናየው ይሆናል ብለዋል፡፡
ግድቡ ከጥንስሱ ጀምሮ የውጭ ሃይላትን ድጋፍ በገንዘብም፣ በፖለቲካም፣ በግብዓትም ታሳቢ አድርጎ የተጀመረ አይደለም፤ እኛ እና እኛን ብቻ ታሳቢ ያደረገ ነው ሰሉ አብራርተዋል፡፡
ስለዚም የምርቃቱን ድል በምናበስርበት ቀን ከጎናችን የሚቆሙ ወዳጆቻችን ይኖራሉ ብለን እንጠብቃለን፤ በዋነኝት ግን የእኛ የኢትዮጵያዊያን ጽናት ውጤት ያመጣበት ሌሎች ታላላቅ ፕሮጀክቶችን መስራት እንደምንችል ያሳየንበት ነው ብለዋል አምባሳደር ነቢያት ጌታቸው፡፡
ኢትዮጵያ የኢነርጂ ዲፕሎማሲ ላይ እየሰራች ነው ያሉት አምባሳደር ነብያት የጋራ ሃብትን በጋራ ማልማት እና መጠቀም ይገባል የሚል ጽኑ እምነት አላት ሲሉ አስረድተዋል።
ግድቡም አፍሪካዊያን በራሳቸው አቅም ሃብታቸውን ማልማት እና መጠቀም እንደሚችሉ የሚያሳይ ፕሮጀክት ነው ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫቸው ጠቁመዋል።
ያሬድ እንዳሻው
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s