ብሔራዊ ቴአትር በመዋቅር ከተፈቀደው ውጪ የዘርፍ ተጠሪነትን ለዋና ዳይሬክተር በማድረጉ ሙያዊ ነፃነቱን አጥቶ በአመራሩ ፍላጎት ላይ መመስረቱን ሪፖርት አረጋገጠ፡፡
- 6 days ago
- 1 min read
ሰኔ 11/2018
የኢትየጵያ ብሔራዊ ቴአትር የሲቪል ሰርቪስ ይሁንታ ሳያገኝ በመዋቅር ከተፈቀደው ውጪ የዘርፍ ተጠሪነትን በቀጥታ ለዋና ዳይሬክተር በማድረጉ ሙያዊ ነፃነቱን አጥቶ በአመራሩ ፍላጎት ላይ መመስረቱን የክዋኔ ኦዲት ሪፖርት አረጋገጠ፡፡
በኢትየጵያ ብሔራዊ ቴአትር፤ የቴአትር አፈጻጸምን በተመለከተ በተሰራ የክዋኔ ኦዲት ተቋሙ ተገቢው ጥናት ሳይከናወን እና የሲቪል ሰርቪስ ይሁንታ ሳያገኝ በመዋቅር ከተፈቀደው ውጭ የቴአትር ጥበባት ምዘናና እና ዴስክ ተጠሪነቱን ቀጥታ ለዋና ዳይሬክተር አድርጓል ተብሏል፡፡
በዚህም ምክንያት ውሳኔው ተቋማዊ ሥርዓቱ እንዲዛባ እና የሚደረገው ምዘና ሙያዊ ነፃነቱን አጥቶ በአመራሩ ፍላጎት ላይ እንዲመሰረት ያደረገ ነው ይላል ዛሬ ለፓርላማ የቀረበው የዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት የክዋኔ ኦዲት ሪፖርት፡፡
ሪፖርቱ ለሙዚቃ እና ለቴአትር ክፍል ትኩረት ተሰጥቶ በሰው ኃይል እንዲሟላ ያልተደረገ መሆኑንም አክሏል፡፡
ለሙዚቃ ክፍል በመዋቅር የተፈቀደው መደብ 181 ሲሆን አሁን በስራ ላይ ያለው የሰው ኃይል ግን 62 ወይም 34 በመቶ ነው ይላል ሪፖርቱ፡፡

ለቴአትር ክፍል በመዋቅር የተፈቀደው መደብ ደግሞ 67 ሲሆን አሁን በስራ ላይ ያለው የሰው ኃይል 32 ወይም 47 በመቶ ነው፡፡
በተጨማሪም የክዋኔ ኦዲት ሪፖርቱ ተቋሙ ከ2015 እስከ 2017 ዓ.ም በጥናትና ምርምር የተገኙ የኢትዮጵያ ብሔሮች ፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ትውፊታዊ ትውን ጥበባት ሥራዎች በአገር አቀፍና በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚዛናዊነት የሚቀርቡበትና የሚታወቁበት ስርዓት ዘርግቶ ተግባራዊ እንዳላደረገ አስረድቷል፡፡
በዚም ምክንያት በተቋሙ የተሰራ ትውፊታዊ ትውን ጥበባት ቴአትር ከአዲስ አበባ ውጭ በአገር አቀፍና በዓለም አቀፍ ደረጃ አልቀረበም ብሏል፡፡
አገልግሎት ለሚሰጥበት የትርኢት አዳራሽ ጥገና እና እድሳት አላደረገም ያለው ሪፖርቱ በዚህም ምክንያት ቁሶች ለአገልግሎት አሰጣጥ ምቹ እና ሳቢ እንዳይሆኑ ማድረጉን ዘርዝሯል፡፡
በቴአትር ቤቱ መድረክ የሚቀርቡ ቴአትሮችና ሙዚቃዎችን ቀርጾ ለማኖር የድምጽ መሳሪያዎች ጥራታቸው ተጠብቆ የሚቀረጹበት፤ በቴክኖሎጂ የተደገፈ የቴአትርና የሙዚቃ መረጃ አሰባሰብና ዘርግቶ ተግባራዊ አላደረገም፡፡
ከ2015 እስከ 2017 ዓ.ም የቴአትርም ሆነ የሙዚቃ ቀረፃ አልተደረገም፡፡
ያሬድ እንዳሻው





Comments