በኢትዮጵያ ሀገራዊ የኤች አይ ቪ ስርጭት ላይ ወጣቶች በተለየ መልኩ በቫይረሱ የመያዝ እድላቸው እየጨመረ ነው ተባለ
- sheger1021fm
- Sep 24
- 1 min read

በኢትዮጵያ ሀገራዊ የHIV ስርጭቱ ካላፉት ዓመታት የተሻለ ቢሆንም ከክልል ክልል ፣ ከከተማ ከተማ የስርጭቱ መጠን እንደሚለያይ ተነግሯል።
ነገር ግን በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ያለው የHIV ስርጭት ካለፉት ዓመታት መቀነስ የሚታይበት መሆኑ መነገሩ የመከላከል ሥራው ላይ መዘናጋትን እንዳይፈጥር ስጋት አለ ተብሏል።
በተለይ በወጣቶች እና ለኤች አይ ቪ እጅግ ተጋላጭ ተብለው የተለዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ላይ የመያዝ እድሉ በመጨመሩ መዘናጋት እንዳያስከትል ጥንቃቄ እንደሚያስፈልግ የጠቆሙት በኤድስ ሄልዝ ኬር ፋውንዴሽን (AHF) ኢትዮጵያ የኤች አይ ቪ መከላከል እና ምክር አገልግሎት አስተባባሪ እንዲሁም የህብረተሰብ ጤና ባለሙያ የሆኑት አቶ ቢኒያም ባዩ ናቸው።
በጠቅላላው የማህበረሰብ ክፍል ውስጥ ያለው የስርጭት መጠን ከዚህ ቀደም ከ 1 በመቶ በላይ ተሻግሮ የነበረውን በትብብር በመሰራቱ የስርጭቱ መጠን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ ቢመጣም በተለይም በስራቸው እና በጾታቸው ምክንያት ተጋላጭ የሆኑ ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ መሆኑንም አቶ ቢኒያም ይናገራሉ።
በወጣቶች በኩል የኤች አይቪ የመያዝ ቁጥርም ከፍተኛ ነው የሚሉት ባለሙያው በኤች አይ ቪ መከላከል ላይ የሚሰሩ አዳዲስ ጥናቶች እነሱ ላይ ትኩረት ሊያደርጉ ይገባል ብለዋል።
በቅርብ የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲቱዩት በሰጠው መረጃ መሰረት በወጣቶች ላይ ያለው የኤች አይቪ የስርጭት ሁኔታ 1.7 በመቶ እንደሚጠጋ የተነገረ ሲሆን ከትምህርት ቤት ውጪ ባሉ ወጣቶች 2.2 በመቶ እና ትምህርት ቤት ያሉ ደግሞ 1.3 በመቶ ነው ተብሏል።
በአጠቃላይ ወጣቶችን ስንመለከት ካለው የኤች አይቪ ስርጭት ሁኔታ ከፍ ያለ መሆኑን እና ከሌላው የማህበረሰብ ክፍል በተለየ ሁኔታ ከ10 እስከ 24 የእድሜ ክልል ላይ ብዙ መስራት እንደሚያስፈልግ በቅርብ ጊዜ እየወጡ ያሉ መረጃዎች እንደሚያሳዩ ባለሙያው ተናግረዋል።
ምህረት ስዩም
ሙሉ ዘገባውን ያድምጡ…. 👇👇👇👇👇
ትኩስ ወሬዎችን ፣ ወቅታዊ መረጃዎችን እና ሙሉ የሸገር ፕሮግራሞችን በቀላሉ ለማግኘት የሶሻል ሚዲያ ፔጃችንን አሁን ይቀላቀሉ።












Comments