top of page

በአለም አቀፍ ደረጃ የለጋሾች ድጋፍ በመቀነሱ ኢትዮጵያን ጨምሮ በምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ዘላቂ ለውጥን ለማምጣት የሚያስችል የበጎ አድራጎት ተቋም መገንባት እንዳለባቸው ተመከረ፡፡

  • 6 hours ago
  • 1 min read

ሰኔ 10/2018


በአለም አቀፍ ደረጃ የለጋሾች ድጋፍ በመቀነሱ ኢትዮጵያን ጨምሮ በምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ዘላቂ ለውጥን ለማምጣት የሚያስችል የበጎ አድራጎት ተቋም መገንባት እንዳለባቸው ተመከረ፡፡


ለዚህም በመንግስትና በግሉ ዘርፍ መካከል ትብብር መፍጠር ሀገር በቀል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን ማጠናከር እና ማስፋፋት እንደሚያስፈልግ ተነግሯል።


ይህ የተነገረው ዛሬ በአዲስ አበባ በተጀመረው የምስራቅ አፍሪካ የበጎ አድራጎት ኮንፈረንስ ላይ ነው።


በመድረኩ የበጎ አድራጎት ዘርፍ ላይ የድጋፍ መቀነስ በተለይ ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ ሀገራት የሚገጥሟቸውን ችግሮች ፣ እየተፈጠሩ ያሉ አዳዲስ ለውጦችና በቀጣናው ዘላቂ ልማት ማምጣት ላይ ያተኮሩ ውይይቶች የሚካሄዱበት እንደሆነ ተነግሯል።


ኢትዮጵያ እንደ ዩኤስኤአይዲ(USAID) ያሉ የእርዳታ ተቋማት የሚደረግ የጤናው ዘርፍ ድጋፍ መቀነስ ተከትሎ ለዘርፋ የሚመደበውን በጀት በመጨመር እንዲሁም የአደጋ ጊዜ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል አሰራር መዘርጋቷ የሚመጡ ችግሮችን በመቋቋም በኩል የከወነቻቸው ስራዎች መሆናቸው በኮንፍረንሱ ተነስቷል።


በተለይም ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ ሀገራት የበጎ አድራጎት ዘርፉ በዓለም አቀፍ ደረጃ እያጋጠሙት ባሉ ፈተናዎች መካከል እንደገና ለመገንባትና ውጤቶችን ለማምጣት የሚያስችሉ የአሠራር ለውጦችን የማጠናከር እና በተለያዩ ድጋፍ በሚፈልጉ ዘርፎች መካከል ጠንካራ ትብብር መፍጠር አለባቸው ተብሏል።


ኮንፈረንሱ በቀጣናው የሚገኙ የበጎ አድራጎት ተቋማት ዘላቂ ገቢ በማግኘት በኩል የሚገጥማቸውን ችግሮች የሚለዩበት፣ ሀገራት በጋራ ለመስራት እና ለውጥ ለማምጣት አስፈላጊ የሆነውን የበጎ አድራጎት አቋማቸውን የሚያጠናክሩበት እንደሆነም ተነግሯል።


ኮንፈረንሱ ለሶስት ቀናት ያህል የሚካሄድ ሲሆን ከ30 በላይ አገራት የተውጣጡ ከ600 በላይ ተሳታፊዎች የተገኙበት ነው።


ከነዚህም መካከል ኢትዮጵያን ጨምሮ ከምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የተወከሉ የበጎ አድራጎት ተቋማት መሪዎች፣ የግሉ ዘርፍ ፣ የመንግሥት የስራ ኃላፊዎች፣ የሲቪል ማህበረሰብ ተወካዮች፣ ተጽዕኖ ፈጣሪ ባለሀብቶች፣ የዲያስፖራ በጎ አድራጊዎች ይገኙበታል ተብሏል።


ምህረት ስዩም

Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2026 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page