በታክስ አስተዳደር ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ ከፍተኛ ትችት ከባለሞያዎች ቀረበበት።
- May 20
- 2 min read
ግንቦት 12/2018
በታክስ አስተዳደር ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ ግብር ከፋይዮች አንዴ የተወሰነባቸውን ግብር መጠን ተገቢ እንዳልሆነ የሚያስረዳ አዲስ ማስረጃ እንዳያቀርቡ መከልከሉ ከፍተኛ ትችት ከባለሞያዎች ቀረበበት።
የገንዘብ ሚኒስቴር በበኩሉ አዲስ ማስረጃ ማቅረብ ሙሉ በሙሉ አልተከለከልም፣ የሚፈቀድብት ሁኔታ አለ ብሏል፡፡
ረቂቁ በአንድ ግብር ዘመን ከሁለት ጊዜ በላይ ቅጣት የተጣለበት የግብር ከፋይ ድርጅት ስራ አስኪያጅ፣ የፋይናንስ ሀላፊ ጨምሮ ሌሎች ተሳታፊዎችን በወንጀል ህግ እንዲጠየቁ የሚያደርግ ነው።

በረቂቅ አዋጁ ላይ ትችቱ የቀረበው የገንዘብ ሚኒስቴር ግንቦት 11 ቀን 2018 ዓ.ም በዋና መስሪያ ቤቱ መሰብሰቢያ አዳራሽ ውስጥ ባካሄደው የባለድርሻ አካላት ወይይት ላይ ነው።
በውይይቱ ላይ የተቋማት የስራ ሃላፊዎች፣ የድርጅት ተወካዮች፣ የግብር የህግ አዋቂዎች እና ባለሞያዎች ተሳትፈዋል።
ሽሂር ሸሞሎ የተባሉ ተሳታፊ በግብር አስተዳደር ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ በአዲስ የተካተተውን "የኢዲስ ማስረጃ" ክልከላን አላስፈላጊ ነው ሲሉ ተችተዋል፡፡
በረቂቁ መሰረት “አዲስ ማስረጃ” ማለት የታክስ ውሳኔ ማስታወቂያ ከደረሰው በኋላ በታክስ ከፋዩ የሚቀርብ አዲስ ሰነድ፤ መረጃ፤ ማስረጃ እና ፍሬነገር መሆኑ ተደንግጓል፡፡
በዚህም መሰረት በመጀመሪያው የታክስ አወሳሰን ሂደት ለታክስ ባለስልጣኑ ያልቀረበ፤ለታክስ ውሳኔ ማስታወቂያው ትክክለኛነት አግባብነት ያለው እና የታክስ መጠን ወይም በታክስ ከፋዩ ግዴታ ላይ መሰረታዊ ለውጥ የሚያስከትል ነው ይላል፡፡
ይህም ቅሬታ፣ ይግባኝ ወይም የውሳኔ ማስተካከያ ጥያቄን የሚያቀርብ ታክስ ከፋይ በታክስ ውሳኔ ወቅት ካቀረበው የተለየ አዲስ ማስረጃን ማቅረብ አይችልም፡፡
ከላይ የተዘረዘረው እንደተጠበቀ ሆኖ በተለየ ሁኔታ አዲስ ማስረጃ የሚፈቅደበትን ሁኔታ ረቂቁ ሲዘረዝር አዲስ ማስረጃ በቅሬታ፣ ይግባኝ ወይም ስህተትን ለማረም በሚቀርብበት ወቅት ተቀባይነት ሊያገኝ የሚችለው መንገድም ዘርዝሯል፡፡
በዚህም ሰነዱ ያለመታየቱ በግብር ከፍዩ የታክስ እዳ ላይ ከፍተኛ ጫናን የሚያስከትል ከሆነ፤ ሰነዱን ታክስ ከፋዩ ያገኘው የግብር ውሳኔ በከተሰጠ በኋላ ከሆነ ወይም ሰነዱ ያልቀረበው አቅም በላይ በሆነ ምክንያት ከሆነ እንደሆነ ደንግጓል፡፡
ታክስ ከፋዩ በታክስ እዳው ላይ ከፍተኛ ጫናን የሚያስከትል አዲስ ማስረጃ ያቀረበ ከሆነ ደግሞ በታክስ ሕጉ መሠረት ሰነዱ በታክስ አወሳሰን ወቅት አስቀድሞ ባለመቅረቡ ምክንያት ሊከፈል ይገባ የነበረውን የታክስ ዕዳ 20 በመቶ ቅጣት ይከፍላል ይላል፡፡
ታዲያ ይህ የድንጋጌ ክፍል ከበለሞያዎች ከፍተኛ ተችት ቀርቦበታል፡፡
አቶ ሽሂር ሸሞሎ ይህ የሀግ ከፍል አገሪቱ ካለችበት እውነታ ጋር አብሮ ስለማይሄድ ቢወጣ ሲሉ መክረዋል፡፡
አቶ ሻሂር የታክስ ስርዓቱን "የመጨረሻ ውስብስብ ነው" የሚያደርገው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የታክስ ባለሥልጣን ምን ኦዲት እንደሚያደርግ አይታወቅም ያሉት ተሳታፊው ይህ ድንጋጌ የአገሪቱ የግብር ስርዓት የሚረብሽ ነው ሲሉ ተችተዋል፡፡
ሌላው የውይይቱ ተሳታፊ በኢዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህግ ትምህርት ክፍል መምህር እና ጠበቃ አቶ አስቻለው አሻግሬ ረቂቁ "ጭካኔ የተሞላበት ነው" ሲሉ ተችተዋል፡፡
በረቂቁ አዲስ ማስረጃን በተመለከተ የተደነገገው "በለፉት 40 ፣ 50 ዓመታት ታይቶ የማይታወቅ ወደኋላ የሚመልስ ነው " ሲሉ ሃሳብ ሰጥተዋል፡፡

ለቀረበው ትችት እና አስተያት ምላሽ የሰጡት በገንዘብ ሚኒስቴር ከፍተኛ አማካሪ የሆኑት አቶ ዋሲሁነ አባተ በበኩላቸው አዲስ ማስረጃ ማቅረብ ሙሉ በሙሉ እንዳልተከለከለ አስረድተው የሚፈቀድብት ሁኔታ መዘርዘሩን ጠቅሰዋል፡፡
ረቂቅ ህጉ እያለ ያለው የኦዲት አሰራሩ ህግን ይከተል ነው ሲሉ አቶ ዋሲሁን አክለዋል፡፡
የታክስ አስተዳደር ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ በንባብ ለታሳታፊው ያቀረቡት አማካሪው ደረሰኝ ባለመስጠት የጣለው አስተዳደራዊ ቅጣት ከነበረበት 50 ሺህ ወደ 100 ሺህ ማደጉን ተናግረዋል፡፡
በአንድ ግብር ዘመን ከሁለት ጊዜ በላይ ቅጣት የተጣለበት የግብር ከፋይ ድርጅት ስራ አስኪያጅ፣ የፋይናንስ ሃላፊ ጨምሮ ሌሎች ተሳታፊዎችን በወንጀል ህግ እንዲጠየቁ የሚደርግ ነው ብለዋል።
ሙሉ ዘገባውን ለማድመጥ….
ያሬድ እንዳሻው
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
Website፡ https://www.shegerfm.com/
YouTube : https://shorturl.at/18TS1
Telegram : https://shorturl.at/68aeK
Facebook፡ https://shorturl.at/tm5Q4
WhatsApp : https://shorturl.at/8vwRx
LinkedIn: https://shorturl.at/Vfe6i
Tiktok : https://shorturl.at/lhYiv
Instagram: https://shorturl.at/9X4S7


Comments