top of page

‘’በመንግስት መሥሪያ ቤቶች ከ16.3 ቢሊዮን ብር በወቅቱ አልተወረራረደም’’ የፌዴራል ዋና ኦዲተር

  • Jun 18
  • 3 min read

የሰኔ 11/2018


በ138 መሥሪያ ቤቶች እና በ18 ቅርንጫፎች በወቅቱ ያልተወራረደ በጠቅላላው ብር ከ16.3 ቢሊዮን ብር በላይ ሂሳብ መኖሩን የፌዴራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ዛሬ ለፓርላማ ያቀረበው ሪፖርት ያሳያል፡፡


ውዝፍ ተሰብሳቢው ሂሳብ ከባለፈው ዓመት ከነበረው ጋር ሲመሳከር በ50 በመቶ መቀነሱን በ65 ገጾች የተሰናዳው የዋና ኦዲተር ሪፖርት ጠቅሷል፡፡


የፌዴራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት የ2017 በጀት ዓመት ሒሳብ የፋይናንሺያል፣ የሕጋዊነት እና የክዋኔ ኦዲት ሪፖርትን በዛሬው እለት በፓርላማ መደበኛ ስብሰባ ላይ ያቀርባል፡፡


በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 190/2002 መሰረት ለውሎ አበልና ለመጓጓዣ የተሰጠ ቅድሚያ ክፍያ ሰራተኛው ሥራውን አጠናቅቆ ከተመለሰ በኋላ በሰባት ቀናት ውስጥ እንዲሁም የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የሒሳብ አያያዝ መመሪያ ለሥራ ማስኬጃ የተሰጠ ቅድሚያ ክፍያ በሰባት ቀናት ውስጥ መወራረድ እንዳለበት ደንግጓል፡፡


ይሁንና ተቋማት በዚህ መሰረት መስራታቸውን ለማረጋገጥ ኦዲት ሲደረግ በ138 መሥሪያ ቤቶች እና በ18 ቅርንጫፎች በጠቅላላው ከ16.3 ቢሊዮን ብር በላይ በወቅቱ ያልተወራረደ ሂሳብ መኖሩ በኦዲቱ መረጋገጡን ሰነዱ አስረድቷል፡፡


ተሰብሳቢ ሂሳቡ በዕድሜ ቆይታ ጊዜው ሲተነተን ደግሞ ከአንድ ወር እስከ አንድ ዓመት ብር 4.6 ቢሊዮን ብር፡፡


ከአንድ ዓመት እስከ አምስት ዓመት 6.6 ቢሊዮን ብር፡፡


ከአምስት ዓመት በላይ እስከ አሥር ዓመት 4.8 ቢሊዮን ብር ፡፡


ከአሥር ዓመት በላይ 154 ሚሊዮን ብር፡፡


ቀሪው ከ5 ሚሊዮን በላዩ ብር ደግሞ የቆይታው ጊዜው የማይታወቅ ነው ተብሏል፡፡


ውዝፍ ተሰብሳቢው ሂሳብ ባለፈው ዓመት ከነበረው ከ32 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ወደ 16 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ወይም በ50 በመቶ መቀነሱ ባለ 65 ግልጽ ሰነድ አስረድቷል፡፡

በዚህ በጀት ዓመት ተሰብሳቢ ሒሳብ ከተገኘባቸው ተቋማት መካከል ከፍተኛውን ድርሻ የያዙት ተቋማት፡-


የጤና ሚኒስቴር 3 ነጥብ 4 ቢሊዮን ፣


የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ብር 1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ፣


የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር 982 ሚሊዮን ብር ፣


የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር 958 ሚሊዮን ፣


የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ 926 ሚሊዮን ብር ፣


የትምህርት ሚኒስቴር 762 ሚሊዮን ብር ፣


የአደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽን ብር 648 ሚሊዮን ብር ፣


የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ብር 593 ሚሊዮን ብር


የዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ውዝፍ ተሰብሳቢ ሂሳብ በወቅቱ አለመወራረድ ለመንግሥት ገንዘብ መባከን ምክንያት ስለሚሆን ሳይሰበሰቡ የተገኙት ሂሣቦች እንዲወራረዱ እና ሊሰበሰቡ በማይችሉት ላይ ደግሞ ከመዝገብ እንዲሰረዙ ለየተቋማቱ በላክነው ሪፖርት ማሳሰቡን ጠቅሷል፡፡


በሌላ በኩል በ2016 እና ከዚያ በፊት አለአግባብ የተፈጸሙ ክፍያዎች ተመላሽ መደረጋቸውን ለማረጋገጥ ኦዲት ሲደረግ እንዲመለስ አስተያየት ከተሰጠበት 21 ነጥብ 5 ቢሊዮን ውስጥ ተመላሽ የተደረገው 31 በመቶው ብቻ እንደሆነ ተዘርዝሯል፡፡


ወደ 15 ቢሊዮን ብር ወይንም 69 በመቶ ተመላሽ ያልተደረገ መሆኑ ታውቋል ይላል ሰነዱ፡፡


የኮምቦልቻ ጉምሩክ ቅርንጫፍ 99 በመቶ ፣ የኤርፖርት ጉምሩክ ቅርንጫፍ 94 በመቶ ፣ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ 80 በመቶ ፣ ምዕራብ አዲስ አበባ ገቢዎች ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት 63፣ የኮምቦልቻ ገቢዎች ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት 42፣ የቃሊቲ ጉምሩክ ቅርንጫፍ 40 በመቶ ፣ የሞጆ ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት 34 በመቶ እና አዳማ ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት 32 በመቶ በግኝቱ ላይ በተሰጠው አስተያየት መሰረት እርምጃ ከወሰዱት መካከል ናቸው፡፡


በ2016 እና ከዚያ በፊት ባሉት በጀት ዓመታት የሂሳብ ኦዲት ግኝቶች የማሻሻያ ሃሳብ መሰረት የተሟላ የሰነድ ማስረጃ ሳይቀርብላቸው ለተፈጸሙ ክፍያዎች ማስረጃ የቀረበላቸው መሆኑን ለማረጋገጥ ኦዲት ሲደረግ በ35 መሥሪያ ቤቶች ማስረጃ ሊቀርብለት ከሚገባው 2ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ውስጥ ማስረጃ የቀረበለት ለ51 ሚሊዮኑ ወይንም ለ1 ነጥብ 8 በመቶው ብቻ ነው ይላል ሰነዱ፡፡


ወደ 2 ነጥብ 9 ቢሊዮን ውይንም 98 ነጥብ 2 በመቶው ማስረጃ ያልቀረበለት መሆኑን ተጠቅሷል፡፡



በግኝቱ ላይ በተሰጠው አስተያየት መሰረት እርምጃ ከወሰዱት መካከል የወራቤ ዩኒቨርሲቲ ሙሉ ሙሉ ሲሆን በተቃራኒው የትምህርት ሚኒስቴር 5 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር ወይንም 1 ነጥብ 3 ከመቶውን ነው ፡፡


የፌዴራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ለተቋማቱ በተሰጠው የኦዲት አስተያየት የተሟላ ማስረጃ ላልቀረበላቸው ሂሳቦች ማስረጃ እንዲቀርብ አልያም ገንዘቡ ተመላሽ እንዲሆን በማድረግ አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወሰዱ ማሳሰቡን አሰረድቷል፡፡



ዋና ኦዲተር በ23 የጉምሩክ እና የገቢዎች ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ውስጥ 6.8 ቢሊዮን ያልተሰበሰበ ቀረጥና ታክስ መኖሩ የፌዴራል አረጋግጧል።


ይህም ከባለፈው ዓመት ጋር ሲመሳከር የ65 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል ተብሏል፡፡


በዚህም መሰረት በ11 የጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ እንዲሁም በ12 የገቢዎች ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ከ4.7 ቢሊዮን ብር በላይ አልተሰበሰብም ይላል ሰነዱ፡፡


የድሬዳዋ ገቢዎች ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት 4 ነጥብ 2 ቢሊዮን ፣ የድሬዳዋ ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት 597 ሚሊዮን ብር እና የባህር ዳር ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት 564 ሚሊዮን ያልተሰበሰበ ቀረጥና ታክስ ካለባቸው ዋነኞቹ መካከል መሆናቸው ተጠቅሷል፡፡


ይህ ችግር የልማት ሥራዎች እንዳይፋጠኑ እንቅፋት ከመሆኑም ባለፈ በገቢ አሰባሰቡ ሂደት ላይ ያለውን የክትትል ክፍተት ያመለክታል ሲል መስሪያ ቤቱ አስረድቷል፡፡


በዚህም ዋናው መሥሪያ ቤቱ እና ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶቹ ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት ግብር ከፋዮች ያለባቸውን ውዝፍ ዕዳውን እንዲሰበስቡ እንደሚገባ አሳስቧል፡፡

የተሟላ የወጪ ማስረጃ ሳይቀርብ በወጪ የተመዘገበ ሂሳብ በተመለከተ በተሰራ ኦዲት ደግሞ በ42 መሥሪያ ቤቶች በጠቅላላው ወደ 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር የተሟላ ማስረጃ ሳይቀርብ ክፍያ የተፈጸመ መሆኑን ሰነዱ ዘርዝሯል፡፡


ከ2016 በጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ843 ሚሊዮን ብር ብልጫ አሳይቷል፡፡


የ2016 በጀት ዓመት ጋር የነበረው 345 ሚሊዮን እንደነበር ያስረዳው ሰነዱ የ2017 ግን ወደ 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ይጠጋል፡፡


በ2017 በጀት ዓመት የተሟላ የወጪ ማስረጃ ሳይቀርብ በወጪ ከመዘገቡት መሥሪያ ቤቶች መካከል የሞያሌ ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ፣ የኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ኢንስቲትዩት፣ የመንግሥት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት፣ የማዕድን ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት እና የማዕድን ሚኒስቴር ይገኙበታል፡፡


ለክፍያዎቹ ተገቢው ማስረጃ እንዲቀርብላቸው መስሪያ ቤቱ አሳስቧል፡፡


በብልጫ፣ በድጋሚ እና አለአግባብ የተፈጸሙ የተለያዩ ክፍያዎች በተመለከተ በ17 መሥሪያ ቤቶች በጠቅላላው 280 ሚሊዮን ብር ክፍያ ተፈጽሟል ይላል ሰነዱ፡፡


ይህም ከ2016 በጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ239 ሚሊዮን ጭማሪ አለው፡፡


ያሬድ እንዳሻው

Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2026 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page