ሰኔ 3 2017 - ኢትዮጵያ ለጸጥታ ተቋማት ከፍተኛ በጀት እንደማትመድብ የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ ተናገሩ፡፡
- sheger1021fm
- Jun 10
- 2 min read

ሚኒስትሩ ይህን የተናገሩት የፌዴራል መንግስት ከአንድ ወር በኋላ ለሚጀምረው የ2018 በጀት ዓመት በቀረበው የ1 ነጥብ 93 ትሪሊዮን ብር በጀት ላይ ለመወያየት በምክር ቤት በተገኙበት ወቅት ነው ፡፡
የምክር ቤት አባሉ ዶ/ር ደሳለኛ ጫኔ ለኢኮኖሚ እና ለማህበራዊ መስኮች የተመደበው በጀት ከጠቅላላ በጀቱ አንፃር ሲታይ ዝቅተኛ ነው ብለዋል፡፡
ለፀጥታ ዘርፍ ለመከላከያ፣ ለፌዴራል፣ ፖሊስ እና ለደህንነት የመደብናቸው ደግሞ በመቶ ቢሊዮን ነው ፡፡
እንደማሳያም በቀረበው የበጀት ረቂቅ ሰነድ ላይ ለመከላከያ 80 ነጥብ 9 ቢሊዮን ፣ ለፌዴራል ፖሊስ 11 ነጥብ 1 ቢሊዮን እንዲሁም ለብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት 2 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ተመድቧል፡፡
በኢሕአዴግ ዘመነ መንግስት ለልማት ማለትም ለመንገድ፣ ለመብራትና ለመሳሰሉት ነው ከፍተኛ በጀት ይያዝ የነበረው አሁን ግን ተገልብጦ ለጸጥታ እና ለደህንነት ዘርፎች ላይ ነው ከፍተኛ በጀት እየመደብን ያለነው Securitized state አልሆንም ወይ? ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
ሌላው የብልጽግና ፓርቲ አባል እና የምክር ቤት አባሉ አቶ ዱቤ ጅሎ በበኩላቸው የአጠቃላይ የፀጥታ ዘርፍ ደመወዝ አለመጠቀሱን ተናግረው በተለይ ለመከላከያና ለፌዴራል ፖሊስ እየተሰራ ያለው ስራ መልካም ነው ግን በገንዘብ አልያም በደሞዝ እነሱም መደገፍ አለባቸው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
አቶ ዱቤ ከህዝብ ጋር የሚገናኝን አካል በሥርዓቱ መያዝ አለብን ብለዋል፡፡
የእነሱን ጉዳይ በደንብ ማየት አለብን፣ መከላክያ ባይኖር ዛሬ እያንዳንዳችን እዚህ ቁጭ ብለን አናወራም ነበር ያሉት አቶ ዱቤ የእነሱ በጀት በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጨመር ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ በበኩላቸው በሰጡት ምላሽ ለፀጥታ ተቋማት የተደረገው ጭማሪ ብዙ አይደለም ያሉ ሲሆን እንዲያውም የተመደበላቸው ከሚያስፈልጋቸው በታች ነው ብለዋል፡፡
ከልማት ፐሮጀክቶች በጀት አንፃር ሲታይም በምንም ተአምር አይነፃፀርም ከዓመት ዓመት ጭማሪያቸውም ዝቅተኛ ነው በምን እንደተነሳም አይገባኝም ብለዋል፡፡
እንዲያውም ኢትዮጵያ ከክልሎች አገራት ጋር ሲነፃፀር ለፀጥታ ዘርፍ የምታወጣው ገንዘብ እጅግ ዝቀተኛ ነው ያሉት አቶ አህመድ ሺዴ አብዛኛው በጀት እየወጣ ያለው ለእዳ ክፍያ፣ ለድጎማ እና ለካፒታል በጀት ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡
ኢትዮጵያ Securitized state እየሆነች ነው ለሚለው ይህ ስህተት ነው አገሪቱ ዴሞክራቲክ ነው ብለዋል ፡፡
ከቀረበው የ2018 በጀት አመት 1 ነጥብ 93 ትሪሊየን ብር ውስጥ ለክልሎች ድጋፍ በጀት የተያዘው 314 ነጥብ 7 ቢሊዮን እንደሆነ ከሰነዱ ተመልክተናል፡፡
ያሬድ እንዳሻው
Comments