ሰኔ 19 2017 - የውጭ ሀገር ስራ ስምሪት ረቂቅ አዋጅ ኤጀንሲዎችን እንደ ወንጀለኛ የሚያይ ነው በሚል የሰላ ትችት ቀረበበት
- sheger1021fm
- Jun 26
- 2 min read
የውጭ ሀገር ስራ ስምሪት ረቂቅ አዋጅ አገናኝ ኤጀንሲዎችን እንደ ወንጀለኛ የሚያይ እና ተቆጣጣሪው መንግስት በገበያው ላይ ከግሎች ጋር ገበያን እንዲሻማ የሚያደርግ ነው በሚል የሰላ ትችት ቀረበበት፡፡
በረቂቅ አዋጁ ላይ ትችቱ የቀረበበት ብትናንትናው እለት በህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት የሰው ሃይል ስራ ስምሪት እና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በአዋጁ ላይ ባካሄደው ይፋዊ የባለድርሻ አካል ወይይት ላይ ነው፡፡
6 ሰዓታትን በፈጀው በዚህ የወይይት መደረክ ላይ የተሳተፉ የኤጀንሲዎች የስራ ሃላፊዎች እና ተወካዮች አዋጁ በሀገሪቱ ያሉ 1,400 ኤጀንሲዎችን ህልውና አደጋ ላይ የሚጥል ነው የሚል ትችት አቅርበውበታል፡፡
ሰራተኛ ምልመላን በተመለከተ አዋጁ ማንኛውም ወደ ውጭ ሀገር ሥራ መሰማራት የሚፈልግ ዜጋ ምልመላ የሚከናወነው ከአንድ ማዕከል አገልግሎት ጀምሮ በተዘረጋው የኢትዮጵያ የሥራ ገበያ መረጃ ሥርዓት በኩል ብቻ መሆን እንዳለበት ይደነግጋል፡፡

ይህን አስመልክተው ሃሳባቸውን የሰጡት አቶ ሚፍታህ አብዱ የተባሉ የውይይቱ ተሳታፊ አዋጁ አደገኛ መሆኑን ተናግረው ፍቃድ ሰጪው አካል በቀጥታ በገበያው ላይ እንዲሳተፍ የሚደርግ ነው ብለዋል፡፡
በአዋጁ መሰረት መንግስት ሰራተኞችን ወደ ውጭ መላክ ይችላል ያሉት አቶ ሚፍታህ ታድያ እኛ እንዴት ብለን ነው ከፍቃድ ሰጪው፣ ተቆጣጣሪው እና ከተደራዳሪው አካል ጋር መወዳደር የምንችለው? ተፎካካሪያችን እኛ የምንፍልገውንስ አገልግሎት እንዴት ብሎ ነው ፍትሃዊ ሆኖ ሊሰጠን የሚችለው? ሲሉ ጠይቀዋል::
እኛ እንደ አልሚ መታየት ሲገባን አዋጁ ግን እኛን እንደ ወንጀለኛ ነው የተመለከተን ሲሉ አቶ ሚፍታህ አክለዋል፡፡
ሌላው የሰላ ትችት የቀረበበት የአዋጁ ከፍል ስለዋስትና ገንዘብና ኢንሹራንስን በተመለከት በተደነገገው ላይ ነው፡፡
በአዋጁ መሰረት ማንኛውም ኤጀንሲ ለሠራተኛው መብት ክብር እና ደህንነት ዋስትና ማስከበሪያ የሚውል ገንዘብ በዶላር ወይም ተመጣጣኙን የኢትዮጵያ ብር በሚኒስቴሩ የባንክ የሂሳብ ቁጥር ማስቀመጥ አለበት ፡፡
በዚህም ለደረጃ አንድ 250,000፣ ለደረጃ ሁለት 200,000፣ለደረጃ ሶስት 150,000፣ ለደረጃ አራት 100,000 እንዲሁም ለደረጃ አምስት 50,000 የአሜሪካን ዶላር ማስቀመጥ እንዳለባቸው አዋጁ ያስገድዳል፡፡
በዚህ ጉዳ ይላይ ሃሳባቸውን ከሰጡት ውስጥ አንዱ እና ለበርካታ ዓመታት በዘርፉ ላይ እንደቆዩ የተናገሩት አቶ ሽመልስ አበበ ናቸው፡፡
ይህ የዋስትና ገንዘብ የተጋነነ መሀኑን የተናገሩት አቶ ሽመልስ አቅማችንን ያገናዘበ እንዲሆን ቢያንስ ለምን ከጎረቤት ሀገራት ተሞክሮ መውሰድ አልተቻለም ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
ለምሳሌ በኬንያ ለዋስትና የሚጠየቀው ገንዘብ 11,000 ዶላር ነው ያሉት ተሳታፊው በዩጋንዳ ደግሞ 28,000 ዶላር ነው ብለዋል፡፡
አብዱልመናን ሁሴን የተባሉ ሌላ ተሳፋፊ በበኩላቸው አዋጁ ሊጠናቀቅ ጥቂት ቀናት በቀሩት በዚህ በጀት ዓመት ከጸደቀ ለበርካታ ሰዎች የስራ እድል የፈጠሩ 1400 ኤጀንሲዎች ህልውናቸው አደጋ ላይ ይወድቃል ሲሉ ተናገረው፤ ጊዜ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡
ለጥያቀዎቹ ምላሽ እና ማብራሪያ የሰጡት የስራ እና ክህሎት ሚኒስቴር ሚኒስትር ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል በበኩላቸው አዋጁ የዜጎችን ክብር ለመጠበቅ የተሰናዳ እንደሆነ ተናግረው፤ ኤጀንሲዎቹን አዋጁ እንደወንጀለኛ ነው የሚያያቸው የሚለው እሳቤ ከየት እንደመጣ ሊገባኝ አልቻለም ብለዋል፡፡

አዋጁ ህጋዊውን መንገድ ተከትሎ የሚሰራውን የሚበረታታ ነው፣ ህገወጡን ደግሞ ተጠያቂ የሚያደርግ ነው ሲሉ ሚኒስትሯ ተናግረዋል፡፡
አዋጁ ከጥቅማቹ ጋር ለምን እንደሚጻርር ሊገባን አይችልም ያሉት ሚኒስትሯ መንግስት የእናንተን ሞኖፖላይዝ የማድረግ ፍላጎት የለውም ሲሉ አስረድተዋል፡፡
በገበያው ላይ ትፎካከሩናላቸው የሚለው አስተሳሰብ ትክክል አንዳልሆነ የተናገሩት ወ/ሮ ሙፈሪያት እኛ ልንፎካከራቹ ሳይሆን እናንተን የሚያደናቅፉ ማነቆዎችን እንፍታላቹ ነው እያልን ያለነው ሲሉ መለስዋል፡፡
የዋስትናውንም ገንዘብም ከፍ ሳይሆን ዝቅ እንዲል ነው ያደርነው ብለዋል ሚኒስትሯ፡፡
በነባሩ አዋጅ ላይ ለዋስትና የተቀመጠው የገንዘብ መጠን 100,000 ዶላር ነው አሁን ግን በ50,000 ዶላር እንዲሆን ነው ያደረግነው ብለዋል፡፡
250,000 ዶላር የተባለው ወደ አንድ ሀገር ብቻ እና ጥቂት ሰው ለሚልክ ኤጀንሲ ሳይሆን ደርጅት ሆኖ ብዙ ሰዎችን ወደ ብዙ ሀገራት ለሚልኩ ነው ብለዋል፡፡
250,000 ዶላር የሚጠየቁት ትንንሽ ኤጀንሲዎችን እና የቤት ሰራተኞችን ለሚልኩ ሳይሆን በትምህርት ዝግጅታቸው ብቁ የሆኑ ሰዎችን ነው ሲሉ ሚኒስትሯ አስረድተዋል፡፡
ያሬድ እንዳሻው
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s
📌 Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il








