ሰኔ 17 2017 - የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ከመጪው አዲስ ዓመት ጀምሮ በሁሉም ክልሎች ይተገበራል ተባለ
- sheger1021fm
- 7 hours ago
- 2 min read
ኢትዮጵያ የቀለጠፈ የመንግስት አገልግሎቶችን እንድሰጥ ያስችለኛል ያለችውን የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ከመጪው መስከረም 2018ዓ.ም ጀምሮ በመላው ሃገሪቱ አሰፋዋለሁ ስትል በ10ኛው የአፍሪካ የመንግስት አገልግሎት ጉባኤ ላይ ተናግራለች፡፡
ከትናንት በስቲያ ቅዳሜ ሰኔ 14 እስከ ዛሬ ሰኞ ሰኔ 16 ቀን 2017ዓ.ም በአዲስ አበባ የአፍሪካ ህብረት መሰብሰቢያ አዳራሽ ሲካሄድ በነበረው 10ኛው የአፍሪካ የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ጉባኤ ኢትዮጵያን ጨምሮ የአባል ሃገራቱ ተወካዮች ተሞክሮዎቻቸውን አቅርበዋል።
በሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን የተወከለችው ኢትዮጵያ ደካማ ሆኖ የቆየውን የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥ ለማዘመን የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም ማድረጓል ተናግራለች፡፡
የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ወ/ሮ አልማዝ መሰለ 124 አገልግሎቶች በአንድ ማዕከል የሚሰጡበትን የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ከሁለት ወራት በፊት ወደ ስራ መግባቱን ጠቅሰዋል፡፡

ከዚህ ቀደም ማድረግ ያልቻልነውና በዚህ አገልግሎት የጀመርነው ሌላው የተገልጋዩን እርካታ መለካት ነው፤በዚህም 92 በመቶ ተገልጋይ በአገልግሎቱ መርካቱን ተረድተናል ያሉት ምክትል ኮሚሽነሯ፤ ይህንን አገልግሎት በማስፋፋት ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ በ12ቱም ክልሎችና በሁለቱም የከተማ አስተዳድሮች ተመሳሳይ የአንድ ማዕከል አገልግሎቶችን የሚሰጡ ተቋማት እንደሚከፈቱም አስረድተዋል፡፡
በጉባኤው የህብረቱ አባል ሃገራት የመንግስት አገልግሎትን ለማዘመን እየሰራን ነው ያሉትን ተናግረዋል፡፡
ከሌላው የአለም ክፍል አንፃር በአብዛኛው የአፍሪካ ሃገራት ለዜጎቻቸው የሚሰጡት የመንግስት አገልግሎት ዝቅተኛ የሚባል ነው ተብሏል።
በሃገራቱ አገልግሎት ፈልጎ የሚሄድን ተገልጋይ ማማረር መገለጫቸው የሚመስሉት የመንግስት ተቋማት በውይይቱ በብዙ ተተችተዋል።
የመንግስት አገልግሎት እንዳይዘምን ምክንያቶቹ በቅኝ ግዛት ውስጥ መቆየታችን፤ ከዚህም ከወጣን በኋላ ወጥ የሆነ የአስተዳር ስርዓት ከመዘርጋት ይልቅ በእርስ በርስ ጦርነት በመጠመዳችን፣ የተረጋጋና አገልጋይ የሆነ የመንግስት አስተዳደር ባለመኖሩ ነው ሲሉ የሃገራቱ ተወካዮች አስረድተዋል።
ውይይቱን የመሩት የደቡብ አፍረካ የፐብሊክ ሰርቪስ ሚኒስትር ዶክተር ማታይዋ ቡሴካ አገልግሎቶቻቸውን ለማሻሻል ሃገራቱ ቢከተሏቸው ተባለውን ዘርዝረዋል፡፡
ዲጂታል ቴክኖሎጂን በመጠቀም በርከት ያሉ አገልግሎቶች በአንድ ማዕከል እንዲሰጡ በማድረግ አገልግሎቶችን ቀልጣፋ፣ ተደራሽና ዘመናዊ የማድረግ ጉዞው በአብዛኞቹ የአፍሪካ ሃገራት ተጀምሯል ያሉት ዶክተር ማታይዋ አብዛኛው የአህጉሪቱ ችግር የሚጀምረው የሪፎርም ትግበራ ላይ ነው፤ ስለሆነም አዚህ ላ ብንበረታ ብለዋል፡፡
ለሶስት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የአፍሪካ የመንግስት አገልግሎት ጉባኤ ከ2 መቶ በላይ የህብረቱ አባል ሃገራት ተወካዮችን እንዲሁም ከመካከለኛው ምስራቅና እስያ የተወከሉ እንግዶች የተሳተፉበት ነበር፡፡
ምንታምር ፀጋው
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s
📌 Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
Opmerkingen