ሰኔ 13 2017 - በኢትዮጵያ ዋነኞቹ ጥላቻ ንግግር አሰራጮች ታዋቂ የሚባሉ ሰዎች እንደሆኑ ጥናት አሳየ።
- sheger1021fm
- Jun 20
- 1 min read
በኢትዮጵያ ዋነኞቹ ጥላቻ ንግግር አሰራጮች ታዋቂ የሚባሉ ሰዎች እንደሆኑ ጥናት አሳየ።
ጥናቱ ያካሄደው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሀን ባለስልጣን ነው፡፡
የማህበራዊ ሚዲያን በመጠቀም ሐሰተኛ እና የጥላቻ ንግግሮችን በከፍተኛ ደረጃ የሚሰራጩት በፁሁፍ እና በተንቀሳቃሽ ምስል እንደሆነም በጥናቱ አሳይቷል።
ሐሰተኛና የጥላቻ ንግግሮች በብዛት የተሰራጩት በፌስቡክ፣ ቴሌግራምና እና ቲክቶክ እንደሆነም ተነግሯል።
ጥናቱ እንደሚያሳየው ከ50 በመቶ በላይ የሚሆነው የጥላቻ ንግግሮች የተሰራጩት ታዋቂ በሚባሉ ሰዎች ነው።
የጥላቻ ንግግሩ ትኩረት ያደረገው ደግሞ በዋናነት የፖለቲካ አመለካከት ባላቸው ሰዎች ላይ እንደሆነም ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በጥናት ለይቼያለሁ ብሏል፡፡

ከፖለቲካ በተጨማሪ ሃይማኖትና ብሄር በሁለተኛ ሶስተኛ ደረጃ መቀመጣቸውን ሰምተናል።
ይህም ፖለቲካን የተመለከተ የጥላቻ ንግግር 77 በመቶ ሲሆን ሃይማኖት ላይ የሚሰነዘሪ ጥላቻ ንግግር 6 በመቶ እና በማንነትና በብሔር ላይ ደግሞ15 በመቶ የጥላቻ ንግግር እና ሃሰተኛ መረጃ እንደሚሰራጭባቸው የተናገሩት በባለስልጣኑ የዋና ዳይሬክተሩ አማካሪ የሆኑት አቶ ታምራት ደጀኔ ናቸው፡፡
ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ እነዚህን አይነት መረጃዎች ለማሰባሰብ ከ1700 በላይ የሚሆኑ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ማነጋገሩን አስረድቷል፡፡
በጥናቱ መሰረት የጥላቻ ንግግርና ሐሰተኛ መረጃዎች አሳሳቢ የሚባል ደረጃ ላይ መድረሱን ካረጋገጠ በኋላ መፍትሄ ናቸው ያላቸውን ጉዳዮች አስቀምጧል፡፡
በዚህም የማህበራዊ ሚዲያ አገልግሎት ሰጪ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ቅርንጫፎቻቸውን እንዲከፍቱና የማህበራዊ ሚዲያ ፖሊሲ እንዲኖር ማድረግ ከብዙ በጥቂቱ ናቸው፡፡
ማርታ በቀለ












Comments