top of page

መስከረም 7 2018 - ታላቁ ህዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያ ከተሞች፣ ኢንዱስትሪዎች ፣ ለግብርና፣ ለእያንዳንዱ ሰው እና ለአየር ንብረት ምን አዲስ ነገር ይጨምራል?

  • sheger1021fm
  • Sep 17
  • 2 min read

ታላቁ ህዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያ ከተሞች፣ ኢንዱስትሪዎች ፣ ለግብርና፣ ለእያንዳንዱ ሰው እና ለአየር ንብረት ምን አዲስ ነገር ይጨምራል?


አክሊሉ ፍቅረስላሴ(ዶ/ር) የአለም ሀብት ተቋም ( world resources institute) የአፍሪካ ዳይሬክተር ሲሆኑ በትምህርት ዝግጅታቸው ደግሞ የከተማ ልማት እና የምጣኔ ሃብት ባለሞያ ናቸው።


የህዳሴ ግድቡ መጠናቀቅ አባይን ለዘመናት ከነበረበት ቅኝ ግዛት ነጻ ያወጣ ነው የሚሉት አክሊሉ(ዶ/ር) ኢትዮጵያ ዘላቂ የልማት ግቦቿን እንድታሳካ ድርሻው ከፍተኛ እንደሆነ አብራርተዋል።

ree

ኢትዮጵያ ብዙ የልማት እና የፈረመቻቸው አለም አቀፍ ግቦች እንዳላት የተናገሩት ዳይሬክተሩ ከዚህ ውስጥ አንዱ የካርቦን ልቀትን ለመቀነስ የገባችው ውል ነው ብለዋል።


በዚህም ህዳሴ ግድቡ አሁን አገሪቱ ካላት ታዳሽ ሃይል ተጨማሪ 5150 ሜጋ ዋት እንድታገኝ ስለሚረዳት ይህም ለብክለት ምክንያት የሆኑ ችግሮችን ለመፍታት እና ለመተካት የማይተካ ድርሻ እንዳለው አብራርተዋል።


ሌላው ኢትዮጵያ ለሚቀጥሉት 50 ዓመታት ለመተግበር ቃል የገባችው low emission sustainable development ለመተግበር ሲሆን ይህም ሀገሪቱ እድገቷ በጭስ የተሞላ ሳይሆን ከብክለት ነጻ እንዲሆን ቃል የገባችውን ለመወጣት ይረዳታል ብለዋል።


ለከተሞች እድገት፡-


እንደ አክሊሉ (ዶ/ር) ማብራሪያ ከተሞች ያለ ሃይል ማደግ አይችሉም።


ካደጉም እድገታቸው ጤነኛ እና ዘላቂ አይሆንም።


በኢትዮጵያ ከተሞች በ5 በመቶ እንደሚያድጉ የሚናገሩት አክሊሉ (ዶ/ር) ይህም በየዓመቱ 1.5 ሚሊዮን ህዝብ ወይም ከሶስት የክልል ከተሞች የህዝብ ቁጥር ጋር የሚስተካከል ሰው ወደ ከተሞች ይገባል።


ይህን እድገት የሚመጥን ሃይል ደግሞ ኢትዮጵያ ያስፈልጋታል ለዚህ ደግሞ ህዳሴ አጋዥ ነው።

ለኢንዱስትሪ እድገት ፡-


ያለ ሃይል ኢንዱስትሪዎችን ለማስፋፋት እንደማይቻል የጠቆሙት አክሊሉ ፍቅረ ስላሴ በተለይ ታዳሽ ሃይል በበቂ ለኢንዱስትሪዎች ማቅረብ ብክለትን ከመቀነስ ባለፈ ለዘላቂ እድገት መሰረት ነው ብለዋል።


በሀገሪቱ በዓመት ከ10 እስከ 15 በመቶ የሃይል ፍላጎት እድገት አለ የሚሉት አክሊሉ ፍቅረ ስላሴ (ዶ/ር) ይህን ክፍተት መሙላት ካልቻልን እድገትን ለማሳካት አስቸጋሪ ይሆናል ሲሉ አስረድተዋል።


ህዳሴ የሚያመነጨው 5150 ሜጋ ዋት ታዳሽ ሃይል ደግሞ ይህን ለመሙላት ይረዳል ብለዋል።


ለማህበረሰብ የኑሮ መሻሻል፡-


ከ45 እስከ 50 በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ መብራት አያገኝም ያሉት አክሊሉ (ዶ/ር) ከህዳሴ ግድቡ የሚመነጨው ሃይል ይህን ክፍተት ለመሙላት ትልቅ ድርሻ አለው።


ማህበረሰብን የታዳሽ ሃይል ተጠቃሚ ማድረግ በከፍተኛ ሁኔታ ኑሮን ለማሻሻል እና ለማቅለል እንደሚረዳ እንዲሁም ገቢያቸውም 30 በመቶ እንዲያድግ ያደርጋል ብለዋል።

ree

ኢትዮጵያዊ ውስጥ ሃይል ከማያገኘው 87 በመቶ የሚሆነው ህዝብ ሃይል የሚያገኘው ከከሰል፣ ከእንጨት ከተለያዩ በካይ ግብዓቶች መሆኑን የተናገሩት ዳይሬክተሩ ከግድቡ የሚገኘው ሃይል ይህን ለመቀነስ ከፍተኛ ድርሻ አለው ሲሉ ተናግረዋል ።


በዚህም ለሃይል እና ለተለያያዩ ምክንያቶች በሚል የሚጨፍጨፍ 100 ሺ ሄክታር ደንን ከመቆረጥ እንደሚታደግ የአፍሪካ ልማት ባንክን ጥናት በመጥቀስ አስረድተዋል።


ለጤና ፡-


በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚመጡ በርካታ በሽታዎችን ለመቀነስ፣ በከስል እና በተለያዩ ጭሶች የሚጠፉ ሕይወትን ያስቀራል።


ኢኮኖሚውም ዘላቂ እንዲሆን ቀጠናዊ የንግድ፣ የዲፕሎማሲ፣ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት እንዲያድግም ታላቁ ህዳሴ ግድብ ትልቅ ድርሻ አለው ሲሉ የአለም ሀብት ተቋም የአፍሪካ ዳይሬክተር አክሊሉ ፍቅረስላሴ(ዶ/ር)ተናግረዋል፡፡



ያሬድ እንዳሻው


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…




Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page