top of page

ሐምሌ 7 2017 - የኢትዮጵያ የሰራተኛ ማህበራት ኮንፌደሬሽን ፓርላማው ፍቃደኛ ከሆነ በስራ መውጫ ስዓት ፌስታል ይዘው ከሆቴል ተመላሸ ምግብ የሚለምኑ ሰራተኞች መኖራቸውን ማሳየት እንደሚችል ተናገረ፡፡

  • sheger1021fm
  • 17 minutes ago
  • 2 min read

ኮንፌዴሬሽን ይህን ያለው በቅርብ ይጸድቃል ተብሎ በሚጠበቀው የፌዴራል ገቢ ግብር ማሻሽያ ረቂቅ አዋጅ ላይ ዛሬ ሰኞ ሐምሌ 7 ቀን 2017 ዓ.ም በህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት የፕላን በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ከባለድርሻ አካላት ጋር ወይይት ባካሄደበት ወቅት ነው፡፡


ከገቢ ግብር ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ ላይ ከሰራተኛው ለመቁረጥ የቀረበው ሃሳብ ውስብስብ የዋጋ ንረትን እና የድህነት መጠንን ያላገናዘብ ከመሆኑም በላይ ማጭበርበር ሳይኖር በአግባቡ ከደሞዙ ግብር የሚከፍለውን ሰራተኛ ከችግር የሚውጣ ሳይሆን ችግር ውስጥ የሚከት እንደሆነ የኢትዮጵያ የሰራተኛ ማህበራት ኮንፌደሬሽን ዋና ፕሬዘዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ ተናግረዋል፡፡


ሰራተኛው በቀን አንድ ጊዜ በልቶ መዋል አልቻለም ያሉት ፕሬዝዳንቱ ምክንያቱ ደግሞ በርካታ ወጪዎች ስላሉበት ነው ብለዋል፡፡


ተቀጣሪው ሰራተኛ ህክምና ሄዶ መታከም የማይችልበት ሁኔታ ላይ ደርሷል ሲሉ ያስረዱት አቶ ካሳሁን እውነት ለመናገር አንድ ሰው በ5 ሺ ብር ደሞዝ ቤት ኪራይ ይከፍላል ፣ ይበላል፣ ልብስ ይለብሳል ፣ ህክምና ይሄዳል ብለዋል፡፡


ህክምናውን እንተው እየጸለየ ይኑር ፤ቤት ኪራይውንም እንተወው በበረንዳ በሰዎች ላይ በጥገኝነት ይኑር ግን በቀን አንድ ጊዜ እየበላ መኖር የለበትም ወይ? ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

አንድ ድርጅት ከትርፉ 35 በመቶ ግብር ይከፍላል ያሉት የኢትዮጵያ የሰራተኛ ማህበራት ኮንፌደሬሽን ዋና ፕሬዝዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ ሰራተኛውም 35 በመቶ ይከፍላል ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? ሲሉ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡


ነጋዴውም፣ ድርጅቱም ከትርፉ ነው እኮ 35 በመቶ የሚከፍለው ሲሉ ያስረዱት አቶ ካሳሁን ሰራተኛው ግን ከትርፉ ሳይሆን ከሚበላው ላይ ነው የሚከፍለው ይህ እንዴት ነው? እኩል ይሆናል ብለዋል፡፡


ስለሰዎች ስናስብ ልማት ለማስቀጠል ነው ያሉት አቶ ካሳሁን ልማት ያለ ሰው ሰው ያለ ልማት ሊኖሩ አይችሉም ሲሉ አስረድተዋል፡፡


ስለዚህም የሰራተኛውንም ጫና የመንግስትን ዓላማ ታሳቢ ያደረገ የግብር ምጣኔ መጣል አለበት ሲሉ ተናግረዋል፡፡


አሁን በማሻሻያው የግብር መነሻ 2000 ሺ ብር ሲሆን ምን ታሳቢ ተደርጎ ነው? ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

አንድ ስልት ሲሰራ ሰውን ማኖር አለበት ያሉት አቶ ከሳሁን ይህ መነሻ ግን ታሳቢ አላደረገም ብለዋል፡፡


ቋሚ ኮሚቴው እንደገና ከሚመለከታቸው ሰዎች ጋር ቢመካከር ሲሉ የጠየቁት አቶ ካሳሁን ፎሎ የኢትዮጵያ ሰራተኞች ኑሮን አልቻሉም፤ ቋሚ ኮሚቴው ፍቃደኛ ከሆነ ከስራ ሲውጡ ፌስታል ይዘው ሆቴል አካባቢ ቆመው ሲለምኑ አብረን ማየት እንችላለን ብሏል፡፡

የገንዘብ ሚኒስቴር በኩሉ አዋጁ በይድረስ ይድረስ የተዘጋጀ ሳይሆን ሁለት ዓመት ጥናት ተሰርቶበት የተዘጋጀ ማሻሻያ ነው ብሏል፡፡


2000 ብር መነሻ የተደረገበት ምክንያት ደግሞ የመክፈል አቅማችን ዝቅተኛ ስለሆነ ነው ሲል አስረድቷል፡፡

መነሻን ከዚህ ከፍ ለማድረግ ቢፈለግ አገሪቱ ያላት ገቢ አይፈቅድም ወደፊት ገቢው እያደገ ሲሄድ ግን መነሻን ከፍ ማድረግ እንደሚችል የገንዘብ ሚኒስቴር ተናግሯል፡፡


የገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ፍቃዱ ሆረታ የኑሮ ውድነቱ ግብር በመክፍል ብቻ የመጣ እንዳልሆነ ተናግረው በኢትዮጵያ ብቻም ያለ ችግር አይደለም ብለዋል፡፡

ሚኒስትር ድኤታው ከውጭ የምናስገባቸውን መዳበሪያ ፣ ነዳጅ እና መሰል ግብዓቶች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በሰዎች ላይ ጫና ይፍጥራል ብለዋል፡፡


ይህን ችግር ለመፍታት ደግሞ መንግስት ደሞዝ መጨመሩን የተናገሩት ሚኒስትር ዲኤታው መንግስት አቅም በፈቀደ መሰረት ድጋፍ አድርጓል ሲሉ አስረድተዋል፡፡

በገቢ ግብር ላይ ያለውም ጫናውን መቀነስ ነው እንጂ ማጥፋ እንዳልሆነ የተናገሩት አቶ ፍቃዱ ሆረታ በነባሩ አዋጅ ላይ መነሳትን ብናመለከት 600 ነው ወደ 2000 ያደገው በውይይት ተደርጎበት ነው ብለዋል፡፡


በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እና የሞያ ማህበራት ተሳትፎ የተደረገ ማሻሻያ እንጂ ዝም ብሎ የመጣ ቁጥር እንዳልሆነም የገንዘብ ሚኒስቴር ተናግረዋል፡፡

የገንዘብ ሚኒስቴር የግብር መነሻው ከተቀጣሪ ሰራተኛ አሁን ካቀረብነው ከፍ ካለ መንግስት ከፍተኛ ገቢ እንደሚያጣ ተናግሮ በተለይ በክልሎች ገቢ ላይ የበረታ ጫና እንደሚያሳድር ተናግሯል፡፡


ያሬድ እንዳሻው


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page